ቀጥታ፡

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ 16 የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሃ ግብሮች መክፈቱን አስታወቀ

ደብረ ብርሃን ጥቅምት 1/2011 ደብረ ብርሃን ዩነቨርሲቲ በ16 የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሃ ግብሮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ። የዩነቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኃይለማሪያም ብርቄ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2011 ዓ.ም ከሚከፈቱ 16 የትምህርት መርሃ ግብሮች መካከል 4ቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ሲሆኑ 12ቱ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪ ናቸው፡፡ የግብርና ምጣኔ ሀብት፣ጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት፣ ገበያ አስተዳደርና ፋርማሲ በመጀመሪያ ዲግሪ አዲስ የሚከፈቱ ፕሮግራሞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እንሰሳት እርባታ፤ አፈርና ውሃ አያያዝ፣ ከተማ ልማትና አስተዳደር ከ12ቱ አዳዲስ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የድህረ-ምረቃ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ነጋሽ ኃይሉ በበኩላቸው ዘንድሮ በሚከፈቱ 12 የሁለተኛ ዲግሪ አዳዲስ ምርሃ ግብሮች ከ270 በላይ ተማሪዎች ለመቀበል መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ አዲስ በተከፈቱት  የመጀመሪያ ዲግሪ አራት ፕሮግራሞች ከ160 እስከ 240 ተማሪዎች  ለማስተማር ታቅዷል፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 3ሺህ 607 አዲስ የሚመደቡ ተማሪዎችን በመቀበል በአጠቃላይ የቅበላ አቅሙን ወደ 32 ሺህ 455 ለማድረስ ዝግጅት ማጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም