በሶማሊያ ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው የተሰዉ የኩባ ወታደሮችን ለመዘከር የአበባ ጉንጉን ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሊያ ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው የተሰዉ የኩባ ወታደሮችን ለመዘከር የአበባ ጉንጉን ተቀመጠ
አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 በሶማሊያ ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው ሲታገሉ የተሰው የኩባ ወታደሮችን ለመዘከር በኢትዮ ኩባ የወዳጅነት ፓርክ የአበባ ጉንጉን ተቀመጠ። 40ኛው ዓመት የካራማራ የድል በዓልና የኢትዮጵያውያን በኩባ የትምህርት ዕድል የተጀመረበት ክብረ በዓል እየተከበረ ይገኛል። ኢትዮጵያ በወቅቱ ወደ አገር ውስጥ ሰርጎ የገባውን የሶማሊያን ጦር ያሸነፈችበት የካራማራ ድል 40ኛ ዓመት ክብረ በዓል ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ.ም እየተከበረ ነው። ኩባ ወታደሮቿን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ በስልጠናና ውጊያ ላይ አሰማርታ ለሰጠችው ድጋፍ እውቅናና ምስጋና ለማቅረብ እንዲሁም የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት ለማጠናከር ታስቦ ነው ክብረ በዓሉ የተዘጋጀው። የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት 40ኛ ዓመት ክብረ በዓል ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ አያሌው ''አገራችን በውስጥ ችግርና በሶማሊያ ጦር ተወራ አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ወቅት ኩባ ወታደሮቿንና የጦር መሳሪዎያ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የማይዘነጋ ውለታ ሰርታልናለች'' ብለዋል። ከድሉ በኋላም በ1970 ዓ.ም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እያደገ በመምጣቱ የኩባ ሪፐብሊክ 5ሺህ300 የኢትዮጵያ ህጻናትና ወጣቶች በ3 ዙር ወደ ኩባ ሄደው ነጻ የትምህርት እድል እንዲያገኙ መፈቀዱን አስታውሰዋል። የክበረ በዓሉ ዓላማም 40ኛው ዓመት የካራማራ የድል በዓልንና ኢትዮጵያዊያን በኩባ ነጻ የትምህርት ዕድል ማግኘት የጀመሩበትን ቀን መዘከር መሆኑን አስታውቀዋል። ሌላው የኮሚቴ አባልና የኩባ ነጻ የትምርት ዕድል ተጠቃሚ አቶ አበራ ንጉሴ ክብረ በዓሉ የሁለቱን አገሮች የግንኙነት ታሪክን በሚያሳይና ምሁራን ባቀረቡት ጥናታዊ ጹህፍና ውይይት መጀመሩን ገልፀዋል። በትግሉ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው ሲታገሉ የተሰው የኩባ ወታደሮችን ለመዘከር በኢትዮ ኩባ የወዳጅነት ፓርክ የአበባ ጉንጉን ሲቀመጥ የኩባ መንግስት ተወካዮችም ተገኝተዋል። በክብረ በዓሉ ላይ ለመታደም የኩባ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር፣ በጦርነቱ ወቅት ከኢትዮጵያዊያን ጎን በመቆም የታገሉ የኩባ የጦር መኮንኖች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ታውቋል።