ቀጥታ፡

የትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ተመሰረተ

አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 የትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ተመሰረተ። ፌዴሬሽኑ ምስረታውን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ትራንስፖርት የአገራዊ ልማትና እድገት የጀርባ አጥንት በመሆኑ የፌዴሬሽኑ ምስረታ የኢንዱስትሪው ምርታማነት እንዲረጋገጥና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች መብትና ጥቅም እንዲከበር አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ዘርዑ በተለይም ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ትራንስፖርተሮች በአገር እድገትና ልማት መስተጋብር የነበራቸው ሚና ከግል ማህበራት ያላለፈ፣ ያልዘመነና በልማዳዊ አሰራር የተገደበ ነው ብለዋል፤ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መስጠት ላይ ክፍተት መኖሩን በማውሳት። በትራንስፖርተሮች በኩል የአደረጃጀትና የስምሪት ደንቦች እንዲሁም በየጊዜው  በሚወጡ መመሪያዎች ላይ ከኢፍትሃዊነት ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች እንደሚቀርቡ የገለፁት አቶ ብርሃኔ አጠቃላይ በዘርፉ የሀብት ብክነት መኖሩንም አስረድተዋል። በዘርፉ የነበሩትን ችግሮች ለመፍታትም የትራንስፖርት ማህበራት ህብረት በመፍጠርና ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ህጋዊ እውቅና በማግኘት የትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን መቋቋሙን ነው አቶ ብርሃኔ የገለፁት። የተመሰረተው ፌዴሬሽን  የትራንስፖርት ባለሀብቶችን በማቀፍ የኢንዱስትሪው ምርታማነት እንዲረጋገጥና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች መብትና ጥቅም እንዲከበር እንደሚሰራም ጭምር ነው የተናገሩት። በቀጣይም አሁን በሥራ ላይ ያሉ የትራንስፖርት ህጎች፣ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሻሻሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ለመንግስት ግብዓት በመስጠት የትራንስፖርት ዘርፉ እንዲዘምን ፌዴሬሽኑ እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት። በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የኢንዱስትሪ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ወርቁ ዓለምነው በበኩላቸው የፌዴሬሽኑ መመስረት ለሠራተኛ መብትና ጥቅም መከበር ካለው አስተዋፅኦ በዘለለ ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ ሚና አለው። ሚኒስቴሩም ለተቋቋመው ፌዴሬሽን በቴክኒክና በክህሎት ዙሪያ የሚደረጉ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም