ቀጥታ፡

የሰላም ጋዜጠኝነት እንደ አንድ የትምህርት አይነት ሊሰጥ ይገባል

አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 የጋዜጠኝነት ትምህርት የሚሰጡ የትምህርት ተቋማት የሰላም ጋዜጠኝነትን እንደ አንድ የትምህርት አይነት ሊሰጡ እንደሚገባ ተጠቆመ። የጋዜጠኝነት ሙያ ለማህበረሰባዊ ልማትና ሁለንተናዊ ዋስትና ጉልህ ሚና የሚጫወተውን ያህል በወጉና በከፍተኛ ኃላፊነት የሚመራው የስነ-ምግባር ደንብ ከሌለው የዚያኑ ያህል የጥፋት መሳሪያ ሊሆን እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ። ያም ሆኖ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን ግጭቶች ተከትሎ በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡት ዘገባዎች ጥንቃቄ የጎደላቸውና ግጭቶቹን ከማርገብ ይልቅ ሊያባብሱ የሚችሉ አቀራረቦችን  ይከተላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአለም ላይ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ነገሮች ላይ ትኩረታቸውን የማድረግ ዝንባሌ አላቸው። በተለይ የግጭት ዘገባዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ጋዜጠኛው በሃላፊነት ስሜት ሊዘግብ እንደሚገባ ገልጸዋል። ጋዜጠኝነት ሁሌም በምርጫና በውዝግም የተሞላ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ጌታቸው ሙያው ሁሌም ህሊናን እና ሙያዊ ብቃትን ተመርኩዞ በሚወሰኑ ውሳኔዎች የተሞላ በመሆኑ ምንጊዜም ጋዜጠኞች ራሳቸውን አብቅተው መገኘት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ለዚህ ደግሞ ከዩኒቨርስቲዎች ባሻገር እያንዳንዱ የሚዲያ ተቋም ለባለሙያዎቹ በሰላም ጋዜጠኝነት ላይ ተከታታይ ስልጠናዎችን መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉትን ግጭቶች ተከትሎ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡት ዘገባዎች ጥንቃቄ የጎደላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። ዘገባዎቹ ግጭቶቹን ከማርገብ ይልቅ ሊያባብሱ የሚችሉ አቀራረቦችን እንደሚጠቀሙ ነው የገለጹት። የዚህ ችግር ዋና መነሻ ደግሞ በተቋማቱና በባለሙያዎቹ ላይ የሚስተዋለው የዕውቀትና የክዕሎት ክፍተት እንዲሁም ግላዊ አመለካከት መሆኑን ነው ያስረዱት። ''ህብረተሰቡን እናገለግላለን እየተባለ የህብረተሰቡን ሰላም የሚሸረሽር ግብዓት ማቅረብ ማንን ሊጎዳ ማንን ሊጠቅም እንደሚችል ማስተዋል የሚያቅተው ሚዲያና የሚዲያ ባለሙያ የዕውቀት ክፍተት ያለበት ነው'' ብለዋል። የግጭት ዘገባዎች ከሌሎች የሚዲያ ዘገባዎች በተለየ መንገድ ጥንቃቄን የሚሻ በመሆኑ መረጃው እውነት መሆኑ ቢረጋገጥም እንኳ ክስተቱ ተጨማሪ ግጭት የማይፈጥርና በህዝቡ ስነልቦና ላይ ጫና የማይፈጥር ስለመሆኑ ጋዜጠኛው ማረጋገጥ አንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። ''መገናኛ ብዙሃን ለሚያገለግሉት ህብረተሰብ ተገቢና ትክክለኛ መረጃ ሊያስተላልፉ ይገባል''ያሉት አቶ ገብረጊዮርጊስ ህገ-መንግስቱ፣ የመረጃ ነጻነት አዋጁ፣ የብሮድካስት አዋጁና አገሪቷ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተቀበለቻቸውን ህጎች እንዲሁም የኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን ለሚያሰራጩት መረጃ መነሻ ሊያደርጉ እንደሚገባም ጠቅሰዋል። ባለስልጣኑ ተቋማቱ አገራዊ መግባባት ያለው የሚዲያ ተቋምና ባለሙያ ለመፍጠር የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ይናገራሉ። መገናኛ ብዙሃኑ ያላቸውን ነፃነት በመጠቀም  የሙያው ስነ-ምግባርን በመከተል የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴት የማይሸረሽሩና አሉታዊ ያልሆኑ ዘገባዎችን ማቅረብ እንደሚገባቸውም አንስተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም