በህገ ወጥ የቡና ንግድ የተሰማራው ግለሰብ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ

75
አምቦ ጥቅምት 1/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን የባኮ ቲቤ ወረዳ ፍርድ ቤት ቡና በህገ ወጥ መንገድ ሲያጓጉዝ በተያዘው ግለሰብ ላይ በሦስት ዓመት የሶስት ወር ጽኑ እስራትና የ50 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ። የወረዳው ፖሊስ የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ሳጅን ረቡማ ጉዲና ለኢዜአ እንደገለጹት ፍርድ ቤቱ በግለሰቡ ላይ ቅጣቱ የወሰነበት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረብ የነበረበት ጥራቱን የጠበቀ 79 ኩንታል ቡና በሕገ ወጥ መንገድ ሲያስተላልፍ በመገኘቱ ነው። ግለሰቡ ባለፈው ሳምንት ከመቱ ወደ አዲስ አበባ በህገ ወጥ መንገድ ሲያጓጉዝ ባኮ ፍተሻ ኬላ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱ መስከረም 29 ቀን 2011 በዋለው ችሎት ረሳድ ናስር የተባለው ግለሰብ ወንጀሉን መፈጸሙ በቀረቡለት የሰነድና የሰው ማስረጃዎች በማረጋገጡም ቅጣቱን ወስኖበታል። ግለሰቡ በሕገ ወጥ መንገድ ሲያንቀሳቅስ የነበረው 61 ሺህ ብር ግምት ያለው ቡና መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም