የምዕራብ አርሲ ነዋሪዎች በሃዋሳ በቃጠሎ የወደመውን ንብረት ለመተካት ድጋፍ እናደርጋለን አሉ - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራብ አርሲ ነዋሪዎች በሃዋሳ በቃጠሎ የወደመውን ንብረት ለመተካት ድጋፍ እናደርጋለን አሉ
ሐዋሳ መስከረም 30/2011 የምእራብ አርሲ ዞን አባገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፤ ቄሮዎችና አመራሮች በሃዋሳ ከተማ በእሳት ቃጠሎ የወደመውን ንብረት ለመተካት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እንደሚሰሩ ገለጹ፡፡ በሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ የሚመራ ልዑክ ዛሬ በከተማው ተገኝቶ የጉዳቱን መጠን በመመልከት አጋርነቱን አሳይቷል፡፡ ትናንት ማምሻው በሃዋሳ ከተማ ''አሮጌ ገበያ'' ተነስቶ የነበረው የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የምዕራብ አርሲ አባገዳዎች፣ ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ቄሮዎችን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች በአደጋው የደረሰውን ጉዳት መጠን ተመልክተዋል፡፡ የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ ደስታ ቦኩሉ በዚህ ወቅት ጎብኚዎቹ ከኢትዮጵያዊነት ባሻገር ለከተማው ባላቸው ጉርብትና በጉዳቱ የደረሰውን ለመጋራት መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ አደጋው በተከሰተ ወቅት የእሳት አደጋ መከላከያ መኪና በመላክ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ አሁንም የጉዳቱ ሰለባ የሆኑትን በመደገፍ ሂደት ከአስተዳደሩና የከተማው ህዝብ ከጎናችሁ ነን ብለዋል፡፡ ''አንዱ ሲጎዳ ቆሞ የሚያይ ማህበረሰብ ውስጥ አይደለም የኖርነው'' ያሉት ከንቲባው፣ የህዝቡን መስተጋብር በማጠናከር ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ የአደጋው መንስዔ ምንም ይሁን ምንም፤ ሰላማችንን ለማይፈልጉ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳንሆን አንድነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል ብለዋል፡፡ የሻሸመኔ ከተማ የአገር ሽማግሌ ሼህ ሃጂ አደም በበኩላቸው በጉዳቱ የተሰማቸውን ኅዘን ገልጸው፣ ''ጉዳቱ የተፈጸመው በጥፋት ኃይሎች ከሆነ፤ የተቃጠሉት እነሱ እንጂ ንብረቱ አይደለም'' ብለዋል፡፡ ሐጂ ኬኖ ዋሪቱ ደግሞ የደቡብ ክልል ህዝብ በኦሮሚያ ክልል ለሚያጋጥም ችግር ቀድሞ ደራሽ በመሆኑ አደጋውን እንደሰሙ ለማጽናናት መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ሰርገኛ ጤፍ ነው አንድነት የሚመራ መንግሥትም ስላገኘን ተግባሩ በወንጀለኞች የተከናወነ ከሆነም ለጠላት ቦታ አንሰጥም የጠፋውን ንብረት በጋራ እንተካለን ብለዋል፡፡ ''በአደጋው የሰው ህይወት አለማለፉ ትልቅ ነገር ነው፤ ንብረት ነገ ሰርተኝ የምንተካው ነው'' ያለው ደግሞ የሻሸመኔ ቄሮዎች ተወካይ ከማል ወልዥ ነው፡፡ ''የሃዋሳ ወጣቶች አካባቢያችሁንና አገራችሁን መጠበቅ ይኖርባችኋል፤በድጋፉ ከጎናችሁ ነን" ብሏል፡፡ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር እሳቱን ለማጥፋት የእሳት አደጋ መኪና ከመላክ ጀምሮ ላደረገው ትብብርና ለሠራተኞቹ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ሁለቱ እህትማማች ከተሞች በቀጣይም በጋራ የሚሰሩበት ህጋዊ ማዕቀፍ እንደሚኖር ገልጸው፣የአደጋው መንስዔ እየተጣራ ነው ብለዋል፡፡ አደጋውን ለመከላከል የተከናወነው ተግባር እንዳይሳካ ያደረጉ አካላትም በህግ የሚጠየቁ ሲሆን ተጎጂዎችን ለማቋቋም በትኩረት ይሰራል፡፡ በቀጣይም ለመሰል አደጋዎች ተጋላጭ ያልሆነና አደጋውን መቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ ገበያ ለመገንባት እንደሚንቀሳቀስ አስታውቀዋል፡፡ የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ጫዊቻ ቃጠሎው የደረሰበት ገበያ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው የከተማው እምብርት መሆኑን አውስተው፣ የወደመው የሃዋሳ ብቻ ሳይሆን የሃገር ሃብት ነው ብለዋል፡፡ የምዕራብ አርሲ አባገዳዎች፣ ሽማግሌዎች፣ ቄሮዎችና አመራሮች ጉዳቱን የራሳቸው አድርገው በመጥታቸው አመስግነዋል። ''መላው የአሮሞ ህዝብ እንደጠየቀን ነው የምንቆጥረው፤ይህም የህዝብ ለህዝብ መስተጋብሩን ያጠናክረዋል'' ብለዋል፡፡