በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የጣና ባህርዳርና ሙገር ሲሚንቶ ጨዋታ ሳይካሄድ ቀረ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የጣና ባህርዳርና ሙገር ሲሚንቶ ጨዋታ ሳይካሄድ ቀረ
አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የጣና ባህርዳርና ሙገር ሲሚንቶ ጨዋታ ሙገር ሲሚንቶ ቴሴራ (የተወዳዳሪዎች መለያ መታወቂያ) ይዞ ባለመቅረቡ ምክንያት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሳይካሄድ ቀርቷል። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች ትናንት ተካሂደዋል። በሳምንቱ መርሃ ግብር መሰረት ባህርዳር ላይ ከጣና ባህርዳር ጋር ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ስፍራው ተጉዞ የነበረው ሙገር ሲሚንቶ ቴሴራ ይዞ ባለመቅረቡ ጨዋታው እንዳልተካሄደ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ ሁለት ቴሴራ ለቡድኖች እንደሚሰጥና ቡድኖችም በጨዋታዎች ላይ ይዘው መገኘት እንዳለባቸው ተናግረዋል። 'ሙገር ሲሚንቶ ከፌዴሬሽኑ የተሰጠውን ቴሴራ በውድድር ደንብ መሰረት በጨዋታው ላይ ይዞ ባለመገኘቱ ጨዋታው እንዳይካሄድ ተወስኗል' ብለዋል። የፌዴሬሽኑ የውድድርና ስነስርአት ኮሚቴ ነገ በሚያደርገው ስብሰባ የጨዋታውን ኮሚሽነር ሪፖርት በማድመጥ ከተወያየ በኋላ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አቶ ተክሉ ገልጸዋል። ትናንት በተደረጉ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር ጥሩ መሻሻልን ያሳየው አዲስ አበባ ፖሊስ ፌዴራል ማረሚያን በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሶስት ለዜሮ ረትቷል። በክልል በተደረገ ጨዋታ ባለሜዳው ወላይታ ድቻ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መከላከያን ሶስት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፏል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረገ አንድ ጨዋታ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚን በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሶስት ለዜሮ ማሸነፍ ችሏል። በኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አራት ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።