ቀጥታ፡

የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራ

አዲስ አበባ መስከረም 30/2011 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ማሻሻያዎችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል። ምክር ቤቱ በዛሬው 54ኛ መደበኛ ስብሰባው በሶስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ምክር ቤቱ የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽንን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በመወያየትም አጽድቋል። ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው። አገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት ማሻሻል በማስፈለጉ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፋት የተወያየ ሲሆን ማሻሻያዎችን በማከል እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል። የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽንን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ በፌዴራል መንግስት አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ስር የሚገኙ ሰፋፊ የመሬት ይዞታዎችን የሚያስተዳድር የህግ ስልጣን የተሰጠው አካል ባለመኖሩ የመንግስት ቁልፍ የመሬት ሃብት ለከፍተኛ ችግር መጋለጡን ጠቁሟል። ይዞታዎቹ ምን ያህል ስፋት እንዳላቸው፣ የት እንደሚገኙ፣ በማን ባለቤትነት እንደሚተዳደሩና ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ የሚታወቅበት የተቀናጀ መረጃም የለም። በመሆኑም መንግስት ከዘርፉ ማግኘት ያለበትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያገኘ ባለመሆኑ ይዞታዎቹ ሰፋፊና በመሃል ከተማ የሚገኙ ቢሆኑም መስጠት የሚገባቸውን አገልግሎት እየሰጡ ካለመሆናቸው ባሻገር ለተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራት ተጋልጠዋል። የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ መፍትሄ ለመስጠት ስርዓት መዘርጋትና ተቋም ማቋቋም በማስፈለጉም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል። ምክር ቤቱም በቀረበው አጀንዳ ላይ ተወያይቶና ማስተካከያዎችን አክሎበት ደንቡ እንዲጸድቅ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። ምክር ቤቱ የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ረቂቅ ደንብ ላይም የተወያየ ሲሆን ግብይቱን ዘመናዊ፣ ፍትሃዊ፣ ተወዳዳሪና ወጪ ቆጣቢ ሊያደርጉ የሚችሉ አሰራሮችና የብቃት ማረጋገጫ ወረቀት አሰጣጥ በሚመለከት የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል። ረቂቁ የአማራጭ የቡና ግብይት አሰራርን፣ የቡና ቁጥጥር አሰራርን፣ የእሸትና ጀንፈል ቡና መገበያያ ስፍራዎች አወሳሰንና አተገባበርን፣ በህገወጥነት ስለተያዘ ቡናና የኮሚሽን አካፋፈልና ሌሎች ጉዳዮችንም ያካተተ ነው። ምክር ቤቱም በቀረበው የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ረቂቅ ደንብ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ማስተካከያዎችን በማከል ደንቡ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም