የጥናትና ምርምር ስራዎች በሴቶች ተሳታፊነት የተቃኙ መሆን እንዳለባቸው ተገለጸ

64
አዲስ አበባ  መስከረም 30/2011 የጥናትና ምርምር ስራዎች  በሴቶች ተሳታፊነት የተቃኙ መሆን እንዳለባቸው ተገለጸ። ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት 12 ወጣት ሴት ተመራማሪዎችን ያሳተፈ አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ እንሰቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰሩ ጥናቶችና ምርምሮች ሴቶችን ያሳተፉ አይደሉም፤ ይህ አውደ ጥናት በዋናነት የተዘጋጀበት ምክንያትም በዘርፉ ያለው ክፍተት ተለይቶ ሴቶችን  ተሳታፊ ለማድረግ ነው። ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰሩ የፈጠራ ፕሮጀክቶች፣ የምርምርና ጥናት ስራዎች ግባቸውን የሚመቱት ሴቶችን ያሳተፉ ሲሆኑ ነውም ብለዋል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ እንዲህ ዓይነት  ዓላማዎችን አንግበው ወደ ማህበረሰቡ እንዲደርሱ የሚሰሩ የፈጠራ፣ የፕሮጀክትና የምርምር ስራዎች እየተደገፉ ሲሆን በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ በኩልም አንድ ፕሮጀክት ተመርጦ እንዲሰራበት መደረጉ ተገልጿል። አውደ ጥናቱም የአፍሪካ ወጣት ሴት ተመራማሪዎችን በማገናኘት እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ በማድረግ፣ስልጠና በመስጠትና ያላቸውን እውቀት እንዲጋሩ በማስቻል በጥናትና ምርምር ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ያስችላቸዋል ተብሏል። እንዲህ ዓይነቱ አውደ ጥናት ገና ጀማሪ ለሆኑ የአንድ አህጉር ሴት ተመራማሪዎች የጋራ ልምድና አቅም የሚፈጥርላቸው ሲሆን በአህጉር ደረጃ በጋራ ፕሮጀክቶችን ቀርጸው ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለመፍጠር ያችላቸዋልም ተብሏል። ተመራማሪዎቹ የተውጣጡት ከኬንያ፣ ከቡሩንዲ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኡጋንዳ፣ ከታንዛኒያና ከሩዋንዳ ሲሆን ስልጠናው የሚሰጣቸውም ከአሜሪካ ፔን እስቴት ዩንቨርሲቲ  በመጡ ፕሮፌሰሮችና ከኬንያ የጥናትና ምርምር ተቋም በተገኙ ምሁራን ነው። አውደጥናቱን ባዮ-ኢኖቬት አፍሪካና አይ ሲ አይ ፒ ተቋማት  በጋራ አዘጋጅተውታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም