በባሌ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ ቡላላ ሐረር በተባለ ቀበሌ በተከሰተ ግጭት የስድስት ሰዎች ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ ቡላላ ሐረር በተባለ ቀበሌ በተከሰተ ግጭት የስድስት ሰዎች ህይወት አለፈ
ጎባ መስከረም 30/2011 በባሌ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ ቡላላ ሐረር በተባለ ቀበሌ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም በተከሰተ ግጭት የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ ገለፀ፡፡ የጎሎልቻ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ እንደገለጸው የግጭቱ መነሻ የአካባቢውን ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አስተጓግለዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የፍርድ ቤት ማዘዣ በማውጣት ለህግ ለማቅረብ ጥረት ሲያደርጉ በነበሩ የፀጥታ አካላትና ሁኔታውን በተቃወሙ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ነው፡፡ በግጭቱ ህይዎታቸው ካለፉ የአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ ችግሩን ለማረጋጋት ወደ ቦታው በተንቀሳቀሱ የአገር መከላከያ ሰራዊትና የአካባቢው ፖሊስ አባላት ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሷል፡፡ ፖሊስ በቀበሌው በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ባደረገው ፍተሻ ህገ ወጥ የጦር መሰሪያ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገር መከላከያ ሰራዊት ተወካዮች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ጉዳዩ ላይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡