ፍኖተ ካርታው በጽንሰ ሃሳብ፣ በተግባርና በክህሎት የጎለበተ ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል-ምሁራን

አዲስ አበባ መስከረም 30/2011 አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ በስርዓተ ትምህርቱ ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ጉድለት በማስቀረት በጽንሰ ሃሳብ፣ በተግባርና በክህሎት የጎለበተ ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል ሲሉ ምሁራን ገለጹ። በኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ የተቀረጸው በ1986 ዓ.ም ሲሆን ይህ ፖሊሲ አሁንም እየተተገበረ ይገኛል። በተግባር ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ በተለይ በትምህርት ተደራሽነት በኩል ያስገኘው ጥቅም የማይዘነጋ ቢሆንም የትምህርት ጥራቱ ላይ ብዙ ስራ እንደሚቀረው በተደጋጋሚ ጊዜ ይነገራል። በዚህም በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ለ15 ዓመት የሚተገበር የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱ ይታወሳል። የትምህርት ስትራቴጂ ማእከል ዋና ዳይሬክተርና የፍኖተ ካርታው ዝግጅት አማካሪ አቶ ስለሺ ጌታሁን ፍኖተ ካርታው ከትምህርት ጥራት አኳያ፣ ከስራ እድል ፈጠራ፣ ከመምህራንና የተማሪዎች ብቃትና የትምህርት ተደራሽነት ላይ ላሉ ክፍተቶች በመሰረታዊነት መፍትሄ ይሰጣል ይላሉ። በተጨማሪም ፍኖተ ካርታው በቅድመ መደበኛ፣ በመደበኛ፣ በ2ኛ ደረጃና መሰናዶ፣ በቴክኒክና ሙያ፣ በከፍተኛ ትምህርት ፣በመምህራን ልማትና የትምህርት አመራር እንዲሁም ፖሊሲውን የሚያሻሽል ነው። በዋናነነት በዚህ ወቅት የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስም ዘመናዊ የሆነ የቴክኖሎጂ ዘርፍን ማሳለጥ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቁ ሙያተኞችን በማፍራት ተወዳዳሪና ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ በአገሪቱ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ በፍኖተ ካርታው ተካቷል። ይህም አገሪቷ በአጭር ጊዜና በመካከለኛ ጊዜ እደርስበታለሁ ብላ ከያዘቻቸው የእድገት ግብ ጋር እንዲናበብ ተደርጎ የሚተገበር ይሆናል ብለዋል። ይህም "ውጤታቸው ዝቅተኛ ብቻ የሆኑ ተማሪዎች በቴክኖክና ሙያ ትምህርት ዘርፍ ተሳታፊ ናቸው" የሚለውን የተዛባ አመለካከት ያስቀራልም ብለዋል። ዘርፉ እንደማንኛውም የትምህርት ዘርፍ በውጤት፣ በተግባርና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያስችላልም ነው ያሉት። በፍኖተ ካርታው መሰረትም  ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል አንደኛ ደረጃ ፣ 7ኛና 8ኛ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ  ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ በማድረግ በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲሆን የታሰበ ሲሆን፤ 6ኛ ፣ 8ኛና 12ኛ ክፍሎች ላይ የመልቀቂያ ፈተና እንዲኖረው ይደረጋል ነው ያሉት። ይህንንም ለመደገፍ የትምህርት ሚኒስቴር በሶስት ተቋማት እንዲመራ በማድረግ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ሚኒስቴር፣ አጠቃላይ የትምህርትና ስልጠና ሚኒስቴር እና የክህሎትና ሥራ ፈጠራ ሚኒስቴር እንዲሆን የሚያደርግ አሰራር በፍኖተ ካርታው መካተቱን አቶ ስለሺ ገልጸዋል። ሌላው የባህል እሴቶችን በሚያጎለብት መልኩና አገር በቀል የሆኑ እውቀቶችን ያካተተ ተደርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ በሌሎች አገራት የትምህርት ስርዓት የታጠረውን የትምህርት ፖሊሲ ይቀንሰዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና በፍኖተ ካርታው ዝግጅት ተሳታፊ የነበሩት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸወ አሁን በስራ ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ "በጽንሰ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ነው" ብለዋል። በመሆኑም ተማሪዎች በትምህርት ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሙያቸውን እንዲያዳብሩ ምቹ ሁኔታ አልፈጠረም ይላሉ። በዋናነትም ተማሪዎች በተመረቁበት የሙያ መስክ የጽንሰ ሃሳብ እውቀት ቢኖራቸውም ሙያቸውን በተግባር ለመደገፍ ብዙ ግዜ እንደሚወስድባቸው ማረጋገጥ ተችሏል ነው የሚሉት። ለዚህም ደግሞ አገሪቷ ከሰው ኃይል ማግኘት ያለባትን የኢኮኖሚ እድገት እያገኘች አለመሆኑንና የዜጎች ኑሮም በሚፈለገው ልክ እንዳይሻሻል አድርጓል። በተጨማሪም በመንግስትና በግል ተቋማት ተቀጥሮ የመስራት ዝንባሌ እንጂ ስራ ፈጣሪ የመሆን ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑን በአብዛኛው ወጣት መስተዋሉንም በጥናቱ መረጋገጡን አክለዋል። የጥናቱ ሃሳቦች ቀርበዋል ሃሳቦቹ ከተተገበሩ አሁን ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ያስወግዳል። ተማሪዎች የጽንሰ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን አንደኛ ጽንሰ ሃሳብ በትክክል እንዲማሩ ያደርጋል፤ የጽንሰ ሃሳብ ክህሎት ከትምህርት ቤቱ ይዘው ይወጣሉ ሁለተኛ ከጽንሰ ሃሳቡ በተጨማሪ ትምህርቱ በተግባር የተደገፈ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል፡፡ በዚህም በጉዳዩ ዙሪያ የዘርፉ ምሁራንን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በአገሪቱ የሚሰጠውን የትምህርት ፖሊሲ በሚመለከት ጥናት መካሄዱን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ በጥናቱ መሰረትም ፖሊሲውን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል። ፍኖተ ካርታው በጽንሰ ሃሳብ፣ በተግባርና በህይወት ዘመን ክህሎት የተቃኘ በመሆኑም የተሟላ እውቀት ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት ምቹ ነው ይላሉ። ተማሪዎች በጽንሰ ሃሳብ ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር የሚቀይሩበትና ሙያቸውን በትምህርት ቤታቸው የሚያዳብሩበት አሰራር በፍኖተ ካርታው እንዲካተት ተደረጓል። ለዚህም ደግሞ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች የትግባር ትምህርቱ ጎን ለጎን ለማስኬድ ከኢንዱስትሪዎችና ከተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር የሚዳብርበት አሰራርን ለመዘርጋት በሚያስችል መልኩ ፍኖተ ካርታው ያካትታል። በትምህርት ስርዓቱ የተካተተው የህይወት ዘመን ክህሎትም እንዲሁ በአኗኗር ዘያቸው ሊኖር ስለሚገባ አመለካከትና አገር በቀል እውቀት በስፋት የሚተገበርበት መሆኑን በመግለጽ። የፍኖተ ካርታውን ጥናት ለማካሄድም በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ 70 የዘርፉ ምሁራን መረጃ በማሰባሰብ የተሳተፉበት ሲሆን ከዚህ ውስጥም 35 የሚሆኑት የጥናት ሂደቱ ላይ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል። በቀጣይም በፍኖተ ካርታው አተገባበር ላይ የባለ ድርሻ አካላት ፣ የመምህራን ፣ የተማሪዎችና የወላጆች ሃሳብ ታክሎበት በውይይት ከዳበረ በኋላ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም