ተቋማቱ ያልተግባቡበት የቢራ ዕድል ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ ያልተግባቡበት የቢራ ዕድል ጨዋታዎች
አዲስ አበባ መስከረም30/2011የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ህግ የአልኮል መጠናቸው ከ12 በመቶ በላይ የሆኑ መጠጦች በመገናኛ ብዙሃን ማስታወቂያ እንዳይሰራላቸው ይከለክላል። ከልክ በላይ እንዲጠጣ የሚገፋፋ ማስታወቂያ ክልክል መሆኑንም ይደነግጋል። ይሁንና በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቢራ ማስታወቂያዎች በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች የዕድል ጨዋታዎችን አካተው በስፋት እየተላለፉ ይገኛሉ። የአንድ ቢራ የአልኮል መጠን ከ12 በመቶ በታች በመሆኑ ህጉን ባይጥስም እነዚህ ማስታወቂያዎች የተጠቃሚውን ቀልብ በሚስብና ጉጉት በሚፈጥር ሁኔታ መተላለፋቸው አግባብ አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ነዚድ ናስር በኢትዮጵያ የቢራ ፍጆታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው የሚገልጹት። ለአብነትም የዓለም ባንክ እ.አ.አ በ2004 ባወጣው ሪፖርት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች በዓመት 0 ነጥብ 9 ሊትር ቢራ ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን በ2015 ግን አሃዙ ወደ 4 ነጥብ 3 ከፍ ማለቱን አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የቢራ ፋብሪካዎቹ በተለያዩ ጊዜ ሳቢና አጓጊ በሆነ መልኩ የሚጠቀሙባቸው ማስታወቂያዎች መሆናቸውንም ይናገራሉ። ማስታወቂያዎቹ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያለው ጫና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ። ''የመጠጥ ፋብሪካዎች የትኛው ህብረተሰብ ለነሱ በደንብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ለይተዋል። ስለዚህ አሁን የምናያቸው ለምሳሌ ሽልማቶች የተሻለ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች ብዙም ፍላጎት አይኖራቸውም፤ በሽልማት ተበረታተው ለመጠጥ አይሄዱም። የሚሄዱት ምንድነው ገቢያቸው ዝቅ ያለ የትምህርት ደረጃቸው ዝቅ ያለ ገቢና ትምህርት በተወሰነ መልኩ ተቆራኝተው ይሄዳሉ። በማስታወቂያውም ታርጌት ማድረግ የፈለጉት ይህን የህብረተሰብ ክፍል ስለሆነ የመዝናኛ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ወደ ከፍተኛ ጠጪነት የሚያሸጋግር ነው።'' እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያው ገለጻ እነዚህ ማስታወቂያዎች በቁጠባ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ''አንድ ሰው ገቢ ይኖረዋል፤ ገቢውን ለፍጆታ ያውለዋል፤ የተወሰነውን ደግሞ ለቁጠባ ያውለዋል። ስለዚህ አልኮል ፣ቢራ ወይም ሌሎችም ፍጆታዎች ናቸው። ማስታወቂያው በራሱ ሰዎችን ይገፋፋል እንዲጠቀሙ እንዲሞክሩት ያልጀመሩ እንዲሞክሩ የጀመሩት ደግሞ በተደጋጋሚ እንዲሞክሩ ስለሚያበረታታ የሚቆጥቡት መጠን ይቀንስባቸዋል፤ ምክንያቱም የተወሰነ ገቢያቸውን ወደ ፍጆታ ስለሚወስዱት።ተጽዕኖው ቀላል አይደለም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ቁጠባን ይጎዳል።'' በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን እየተላለፉ ያሉት የቢራ ማስታወቂያዎች ተገቢ አለመሆናቸውን ያምናሉ። ''ይሄ ነገር የማስታወቂያ አዋጁ ከሚለውም የሚቃረን ስለሆነ በብሮድካስት አዋጁም መሰረት የዜጎቸን ደህንነት ለመጠበቅ የሚደረገውን የማስታወቂያ ይዘት የማስተካከል ጉዳይም ጭምር የሚጋፋ በመሆኑ ልክ ሊበጅለት ይገባል። ስለዚህ በሎተሪ ስም ሰዎችን ወጣቶችን በተለይ ወደ ጠጪነት የሚገፋ ስለሆነ መላ ሊበጅለት ይገባል በሚል በርካታ ጊዜዎች ንግግር አድርገናል። ከዚህ በተረፈ ግን ባለስልጣኑ ተገቢ እንዳልሆነ ያምናል።'' ማስታወቂያዎቹ ህብረተሰቡ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ከሆነ ባለስልጣኑ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መሰረት ምን እርምጃ ወስዷል? ለሚለው ጥያቄም ምላሽ አላቸው። ''ባለድርሻ አካላት በሚሰሩት ስራ ላይ ጣልቃ ገብቶ ማገድ ማለት መንግስታዊ ስራን ማገድ ጭምር ነው። ይህን የማድረግ ስልጣን የለውም። በሌላ መልኩ ደግሞ ብሮድካስተሮች ሃላፊነታቸው ይሄ እንደሆነ ያውቃሉ። ጥያቄው ምንድነው? ያለው የሎተሪ ዕጣዎች የማወዳደር ስራ ፍቃድ እየሰጠ ያለ አካል ይሄ ከማስታወቂያ አዋጁ አንቀፅ 26 ተራ ቁጥር 3 ጋራ የሚጋጭ መሆኑን የመገንዘብና ለዚያ ተግባራዊነት የመገዛትና ያለመገዛት ጉዳይ ነው። እንደ ብሮድካስት ባለስልጣን መደረግ ያለበትን አድርገናል። ከአምራቾችም ጋር ተግባብተናል፤ ተነጋግረናልም። ከብሔራዊ ሎተሪም ጭምር እዚያ ድረስ ሄደን አነጋግረናል፤ ሃላፊነትን ወስደን እኛ በሃላፊነት መንፈስ እንዲሰራ ተገቢውን ጥረት እናደርጋለን ባሉት ላይ የመሄድና ያለመሄድ ጉዳይ ግን የእነርሱ ነው ጣልቃ ገብነት ነው የሚሆነው ከዚያ ባሻገር ያለው።'' የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ በበኩላቸው አስተዳደሩ ለዕድል ጨዋታዎች ከሚሰጠው ፍቃድ ውስጥ አንዱ የፕሮሞሽን ፍቃድ መሆኑን ይገልጻሉ። የዚህ ፍቃድ ዋነኛ ዓላማ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶችን ለማስፋፋትና ለማስተዋወቅ ነው ብለዋል። አስተዳደሩ ለዚህ የዕድል ጨዋታ ፍቃድ ሲሰጥ በአገሪቷ ያለውን ዝቅተኛ የቢራ ፋብሪካዎች ለማበረታታት መሆኑን በመግለጽ። ''የቢራ ፋብሪካዎች በአገሪቱ ደረጃ በእርግጥስ ተስፋፍተዋል ወይ? አሁን ባላት የኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት አንጻር በእርግጥስ ብዙ ፋብሪካ አለ ወይ? ይህን መመለስ ይጠይቃል። አሁን ላልሽው ጥያቄ ኮንሳምሽኑስ ቢሆን በእርግጥስ ካለው የህዝቡ ብዛት አንጻር ብዙ ነው ወይ? ይህን መመለስ ያስፈልጋል። የሚጠጣውም የቢራ መጠን ሄክቶ ሊትሩ ከአፍሪካ ምን ያህል ደረጃ ነው? የፋብሪካዎቹ ብዛት ራሳቸው ኢትዮጵያ አሁን ከሚያስፈልጋት መጠን ጋር ብዙ ነው ወይ? ይህን መመለስ ያስፈልጋል። ይሄ እኔ እንደሚመስለኝ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለው ይሄ ዕድል ጨዋታ እንዲህ አይነት ምርቶች አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ዕድል የሚሰጥ ነው።'' በአገሪቷ ያሉት የቢራ ፋብሪካዎች ዝቅተኛ በመሆናቸው የዕድል ጨዋታዎቹ በህብረተሰቡ ላይ ማህበራዊ ተጽዕኖን እንደማያመጡም ነው አቶ ቴዎድሮስ የተናገሩት። በአሁኑ ጊዜ የዕድል ጨዋታዎቹ በህብረተሰቡ ላይ እያደረሱ ያሉትን ጫና የሚያሳይ መረጃ ከመጣም ብሔራዊ ሎተሪ አስፈላጊውን ማስተካከያ ያደርጋል ብለዋል። አሁን ባለው የፋብሪካዎች ዝቅተኛ መጠን ግን የቢራ መጠጥ ላይ የተጀመሩት የዕድል ጨዋታዎች ትክክል ናቸው ይላሉ። ''ፋክት ይምጣና በትክከል መረጃ ይምጣና ከዚያ በኋላ ወደ መመሪያ ሄዶ የሚስተካከል ነገር ነው። ያልተጨበጠ ነገር ግን ምን ብለሽ ነው ህጋዊ ነገር የማትሰሪው። ስለዚህ እኛ አንድ በህግ የተቀመጠ ነገር ነው የምንሰራው ሁለተኛ የአገርን ምርት የሚያሳድግ ስራ ነው እየሰራን ያለነው አሁን በጣም በዝቅተኛ የፍጆታ ደረጃ ያለን ጉዳይ ከአፍሪካ ደረጃ ስናነጻጽረው ይምጣና ፋክቱ እንነጋገርበት።'' አቶ ቴዎድሮስ ይህን ይበሉ እንጂ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በሎተሪ ስም የሚደረጉ የቢራ ማስታወቂያዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን እንደሚፈጥር ለአስተዳደሩ ማሳወቁን ነው የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ የሚገልጹት። ሁለቱም ተቋማት የቢራ ሎተሪ ጨዋታዎቹ በህብረተሰቡ ላይ በሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ላይ የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው ከምላሻቸው መረዳት ተችሏል። በማስታወቂያ አዋጁ አንቀጽ 26 ተራ ቁጥር 3 ላይ በተደጋጋሚ ወይም ከልክ በላይ እንዲጠጣ የሚገፋፋ ማስታወቂያን በመገናኛ ብዙሃን ማስተላለፍ ክልክል መሆኑ ተቀምጧል።