ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ግዕዝን በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ሊያስተምር ነው

ደሴ መስከረም 30/2011 የወሎ ዩኒቨርሲቲ  ከያዝነው የትምህርት ዘመን ጀምሮ ግዕዝን በመጀመሪያ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን ለመጀመር በቀረጸው ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ ከምሁራንና ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ተወያይቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊና ሥነ ሰብእ ኮሌጅ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ተጠሪ ዶክተር እንድሪስ ዓቢይ እንዳስረዱት ግዕዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የላቀ ሥፍራ አለው፡፡ ትምህርቱን ለማስጀመር አራት መምህራን የተቀጠሩ ሲሆን ፣እስከ 18 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል። ሥርዓተ ትምህርቱ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ አገር በቀል ህክምናና መድኃኒት፣ የሥነ ከዋክብት ቀመርና የቀን አቆጣጠር፣ የባህልና የህግ ሥርዓቶች ተካተውበታል። ትምህርቱ በቋንቋው የተጻፉ ሥራዎችን ወደ ሌሎች አገርኛ ቋንቋዎች በመተርጎም ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል ዶክተር እንድሪስ ተናግረዋል። በቋንቋው በፍልስፍና፣ በህክምና፣ በሥነ ከዋክብትና በመሳሰሉት የዕውቀት ዘርፎች በርካታ ጽሁፎች ቢጻፉም፤ ህዝቡንም ሆነ አገሪቱን መጠቀም የሚገባቸውን ያህል አልተጠቀሙበትም፡፡ ዕውቀቱም ለሌሎች ሳይተላለፍ ለረጅም ዓመታት መቆየቱን ተጠሪው ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ትምህርት ክፍል አስተባባሪና መምህር አቶ ዘላለም ጌትነት በበኩላቸው የመጥፋት አደጋ ላይ የሚገኘውንና የእውቀት ምንጭ የሆነውን ቋንቋ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መስጠቱ ታሪክን ከማቆየትና እውቀትን ከማጋራት አንጻር ጠቀሜታው ጉልህ ነው ብለዋል። ሥርዓተ ትምህርቱ በተለይ ቋንቋው ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ያለውን ቁርኝት በሚያሳይ መልኩ ቢቀረጽ የተሻለ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህርና የሥነ ጥበባት ኮሌጅ የድህረ ምረቃ ተባባሪ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ "ዩኒቨርሲቲው የአገር ሃብት የሆነውን የግዕዝ ቋንቋ ለማስተማር መወሰኑ የሚያስመሰግነውና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ኃላፊነት እንዲወስዱ መነቃቃትን የሚፈጥርላቸው ነው" ብለዋል፡፡ ግዕዝ ኢትዮጵያን የምናውቅበት የዕውቀት ምንጭ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህንን መገናኛ ብዙኃን አገራዊ ፋይዳ ያለውን የዕውቀት ዘርፍ በማስተዋወቅ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ተማሪዎችን ካስመረቀ በኋላ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከር እንዳለበትም አቶ አሰፋ አሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ወሎ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መአምራን ብርሃነህይወት እውነቱ ቋንቋው በዩኒቨርሲቲው መሰጠቱ በርካታ አገራዊ ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ መንፈሳዊና ዓለማዊ ሥራዎች፣ ምርምርን የሚጋብዙ ሥራዎች  ለማወቅና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በአዲስ መንፈስ ለማስቀጠል  ጠቀሜታ እንዳለው  አስረድተዋል፡፡ የአብነት ተማሪዎች እንቅስቃሴ መዳከም ቋንቋውን እንዳዳከመው አውስተው፣ ዩኒቨርሲቲው የጀመረው ጥረት እንዲሳካ ቤተክርስቲያኗ ድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የቅበላ አቅም ዘንድሮ ከ20 ሺህ በላይ ደርሷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም