አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተስፋዎቹና ፈተናዎቹ

1283
በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ) አንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የተማረ የሰው ኃይል አቅም ነው፡፡ ዛሬ በሣይንስና ቴክኖሎጂ በልጽገው በአገራቸው ልማትን በማምጣት የሕዝባቸውን ተጠቃሚነት ያጐለበቱ አገሮች ልምድ የሚያሳየን ይህንኑ ሐቅ ነው፡፡ በተለይ በቅርብ አመታት ከነበሩበት የድህነት አረንቋ ወጥተው ከፍተኛ የሣይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ላይ የደረሱ የደቡብ ኮሪያ፣ የቻይና፣ የሲንጋፖር፣ የቬትናም፣ የማሌዢያ፣ ወዘተ. አገሮችን ተሞክሮን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ አገሮች ለትምህርትና ሥልጠና በሰጡት ትኩረት የሰው ኃይል ሀብታቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማልማት ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ የሕዝባቸውን ኑሮ ማሻሻል ችለዋል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ትምህርትና ሥልጠና ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት አደረጃጀት ታሪክ በአጭሩ ኢትዮጵያ ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ክርስትናን የተቀበለች በመሆኗ፣ ምናልባትም እስልምናን በመቀበል የቁርዓን ትምህርት ከሚሰጥበት የምሥራቁን የአገሪቱን ክፍል ሳይጨምር በተቀረው ክፍል ለ1,500 ዓመት ያህል በቤተ ክርስቲያኑ ቁጥጥር ሥር የሚካሄድ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ትምህርት ይሰጥባት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ምንም እንኳን በ1900 ዓ.ም. አካባቢ የወቅቱ ንጉሥ የነበሩት ዳግማዊ ምንሊክ የምዕራባዊያን የትምህርት ዘይቤን የተከተለ የትምህርት ተቋማት ቢፈጥሩም፤ ትክክለኛው እና ዘመናዊ የትምህርት አደረጃጀት በኢትዮጵያ የተጀመረው ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የወቅቱ ንጉሥ በነበሩት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደነበር የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በወቅቱ  ዘመናዊ ትምህርትን  ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም እንኳን፣ በ1960 ዓ.ም. አካባቢ ዕድሜያቸው ከሰባት እስከ 12 ከሚደርሱ ተማሪዎች መሀል ከአሥር በመቶ በታች የሆኑት ብቻ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኙ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ለማቀላጠፍ እንዲረዳ በማሰብ ከ400 በላይ የሚሆኑ ‹የሰላም ጓድ› በመባል የሚታወቁ መምህራን ከአሜሪካ በበጎ ፈቃደኝነት በ1962 ዓ.ም. አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት እንዳገለገሉ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የመጀመርያ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ኮሌጆች በ1942 ዓ.ም. አካባቢ መሥራት ጀምረው ነበር፡፡ በ1962 ዓ.ም. ቁጥራቸው 2,800 ያህል የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአገር ውስጥና ወደ ውጭ አገር በመላክ በትምህርት ላይ እንደነበሩ  መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በ1967 ዓ.ም. ወታደራዊው ደርግ የመጨረሻውን የንጉሥ አገዛዝ በመጣል አዲስ መንግሥት አቋቋመ፡፡ አዲሱ ወታደራዊው ደርግ የሶሻሊስት መንግሥትን በመመሥረት ሥርዓቱን ሶሻሊዝም በማለት የሥርዓተ መንግሥቱን ዕምነት በመላው ኅብረተሰብ ውስጥ ለማስፈን ችሎ ነበር፡፡ የመንግሥቱ የትምህርት ዓላማዎች በአጭሩ ሲገለጹ፣ ትምህርትን ለማምረቻ መሣሪያነት መገልገል፣ ትምህርትን ለሳይንሳዊ ንቃተ ህሊና ማዳበሪያነት መገልገል፣ ትምህርትን ለማህበራዊ ንቃተ ህሊና ማዳበሪያነት መገልገል የሚሉ ነበሩ፡፡ ወታደራዊው መንግሥት ፖለቲካዊ ኅብረትና ስምምነት ከሶቪየት ኅብረት ጋር ፈጥሮ ስለነበር የሥርዓተ ትምህርቱ ማሻሻያ ከዚሁ የስምምነት ተፅዕኖ ሥር ወድቆ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ጎልቶ እንዲወጣ የተፈለገው የፖሊ ቴክኒክ የትምህርት አደረጃጀት በሶቪየት ኅብረት መንግሥት አማካሪዎች እንዲቋቋም በማድረግ፣ ምርትን በተፈላጊው መጠን ለማሳደግና ተማሪዎችን በተግባራዊ ሙያ በተሻለ ለማበልጸግ በሚረዳ መልኩ እንዲቋቋም በማሰብ እንደነበር ከታሪክ ድርሳናት የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ በቁጥር እጅግ የበዙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች የአገሪቱን የሰው ሀብት ችግር ከመሠረቱ ለመቅረፍ በተለያዩ የሕክምና፣ የእርሻ፣ የኢንጂነሪንግ፣ የአስተዳደር፣ የኢኮኖሚክስ፣ ወዘተ የዕውቀት መስኮች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሠለጥኑ ሶቪየት ኅብረትን ጨምሮ በሌሎችም በሁሉም ሶሻሊስት በሆኑ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችና ኩባ ተልከው ተምረዋል፡፡ ወታደራዊው መንግሥት ከሥልጣን በኃይል እስከ ወረደበት ጊዜ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ከ1942 ዓ.ም. ጀምሮ በተዋቀረበት ዘዴ ተማሪዎች ትምህርት በሰባት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምረው ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ እስኪገቡ ድረስ ለ12 ዓመታት ትምህርትን በአንደኛ ደረጃ፣ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃና ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ እየተማሩ እንዲቆዩ ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በ1983 የኢህአዴግ መንግሥት ስልጣኑን ከተረከበ ማግስት በ1986 ዓ.ም. የትምህርትና ሥልጠና ፖሊስ በመቅረጽ ባለፉት 24 አመታት ሰብአዊ ሀብትን በማልማት ሀገራችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው፤ ሩቅ ባልሆነ ጊዜም ከበለፀጉት አገሮች ተርታ ማሰለፍ መሠረታዊ መሆኑን በመረዳት ለትምህርትና ሥልጠና ልዩ ትኩረት በመስጠት ሲሰራ መቆየቱን የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ተናግረዋል። በትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው የተቀመጠውን አላማና ግብ ለማሳካት ባለፉት አመታት የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ አግባብነትና ጥራት ለማጐልበት ሰፊ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየቱን ነው ሀላፊው የገለጹት፡፡ በስራ ላይ የነበረው ይህው ፖሊሲ የትምህርትን ሽፋን እንጂ የጥራትን ስታንዳርድ የማያሟላ ሆኖ በመገኘቱ፤  አገር አቀፍ የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ ጥናት ከሚመለከታቸው የባለድረሻ አካላት ጋር በመሆን ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ለ24 ዓመት ሲሰራበት የቆየውን የትምህርት ፖሊሲ ብዙ ክፍተቶች የነበሩበት መሆኑን ፣ ብቁ ዜጋን ለመፍጠር አለመቻሉን ተጠቅሶ የትምህርት ማሻሻያ አዲስ ፍኖተ-ካርታ እንደሚያስፈልግ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትረ ዶክተር አብይ አህመድ መናገራቸውን ተከትሎ ነው  ጥናቱ የተጀመረው።   የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታው ዝግጅት ታሪካዊ ዳራ አንድ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን ከሚያስችሉ ጉዳዮች ዋናውና ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስደው እቅድ ነው፡፡ በተደራጀና ሙሉዕ በሆነ እቅድ የሚሠራ ሥራ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ይህ የፍኖተ ካርታ ሥራ ሦስት ደረጃዎች የያዘ እና የአገር ውስጥ ምሁራን (የአማካሪዎች) ያቀፈ እንዲሆን በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል። የመጀመሪያው ቡድን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ስድስት አባላት ያሉት ዋና ተመራማሪዎች ቡድን መሪዎች ሲሆኑ ዋና ተግባራቸው በስድስት የተለዩ ዋና ጉዳዮች ማለትም ቅድመ መደበኛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት፤ ሁለተኛና መሰናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና፤ የከፍተኛ ትምህርት፣ የመምህራን ልማት፣ እንዲሁም የትምህርትና ሥልጠና አመራርና ፖሊሲ ጉዳዮች የጥናትና ምርምር ማካሄድና በሚገኘው ውጤት ለፍኖተ-ካርታ ሥራው የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ጭብጦች መለየትና ማዘጋጀት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሁለተኛው ቡድን በዋና አጥኚዎች የሚመሩ በተለዩት ዋና ዋና ጉዳዮች ሥር አምስት፣ አምስት ባለሙያዎች በጥቅሉ 36 ዋና አጥኚዎችንና ባለሙያዎችን የያዘ የአጥኚዎች ቡድን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስድስት ቡድኖችን በመስክ መረጃ በማሰባሰብ 73 ረዳት አጥኚዎችና እና 11 ከየክልሉ የተውጣጡ የትምህርት ሃለፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ የአጥኚ ቡድኖቹና የረዳት የባለሙያዎቹ ዋና ዋና ተግባራት በተቀረፀው የጥናት ዘዴዎች አማካኝነት በተመረጡ ክልሎችና የትምህርት ተቋማት በመገኘት መረጃዎችን በማሰባሰብና በማጠናቀር የተገኘውን ውጤት ሪፖርት በማዘጋጀት ለዋናው ተመራማሪ ማስረከብ ነው፡፡ ሦስተኛው አራት አለም አቀፋዊ ባለሙያዎችን የያዘ ሲሆን በዋና አማካሪዎች በተካሄደው ጥናት የሚገኙትን ጭብጦች መሠረት በማድረግ ፍኖተ-ካርታውን ለሕትመት ዝግጁ ማድረግ ሲሆን ይህ የአለም አቀፍ ባለሙያዎች መረጣና ሥራ በሂደት ላይ ያለ ተግባር እንደሆነ ነው የጥናቱ አማካሪ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ የተናገሩት፡፡ በፍኖተ ካርታው ውስጥ የተካተቱ ወሳኝ ለውጦች እና ተስፋዎች ሰነዱ ዘርፉ የገጠመውን መጠነ ሰፊ ተግዳሮት በነቂስ ይዘረዝራል፡፡ የፈውስ መጀመርያ በሽታን ማወቅ በመሆኑ፣ የዘርፉን ችግሮች አብጠርጥሮ ለማስቀመጥ ልዩ ትኩረት መደረጉ በጣም ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥትም የትምህርት ዘርፉ ከገባበት ችግር ለማውጣት በቁርጠኝነት ለማሰራት ሙሉ ፍላጎቱን በማሳየቱ ከሶስት አመት በፊት  ወደ ስራ ተገብቷል። አዲሱ የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የዘርፉን ችግሮች አብጠርጥሮ ለማስቀመጥ ልዩ ትኩረት ማድረጉ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም። የትምህርት ሥርዓቱ በተደራሽነት፣ በፍትሐዊነት፣ በጥራትና አግባብነት አኳያ ስር የሰደደ ችግር ያለበት መሆኑ በማስረጃ ተደግፎ የቀረበ ነው። የጥናቱ ሰነድ እንደሚያመለክተው መንግስትም የትምህርት ዘርፉ ከገባበት ችግር ለማውጣት ቁርጠኛ መሆኑን ያስረዳል። ይህም ለአገራችን የሰው ሃይል ብቃት ተገቢ ሚና ሊጫወት የሚችል ነው። በዚህ መሰረትም የትምህርት ስልጠናው የማሻሻያ ሃሳቦች በርካታና ወሳኝ ለውጦችን እንዲይዝ ተደርጓል። የትምህርት ስርዓቱ ፍልስፍና እና መዋቅር ለመከለስ፣ የመምህራንን ብቃት ለማሳደግ፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ትስስር ለማጠናከር እንደታሰበ ሰነዱ ያስረዳል። ሰነዱ 70/30 የሚለው የመስክ ምጥጥን ፖሊሲ ቀርፆ ጉዳዩ በገበያና በፍላጎት እንዲመራ፣ የወጪ መጋራት ድርሻ በ15 ዓመታት ውስጥ ከ15 በመቶ ወደ 30 በመቶ ከፍ እንዲል፣ የቋንቋ ትምህርት ፖሊሲው እንዲሻሻል፣ የሙያ ምዘና ሥራ ላይ እንዲውሉ፣ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ ዋና አጀንዳ ሆኖ እንዲቀጥል፣ የተግባር ልምምድ በሰፊው ስራ ላይ እንዲውል እና ተማሪዎች በየአመቱ ከ2 እስከ 3 ወር ኢንተርንሺፕ እንዲወጡ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ብዝኃነትን በሚያዳብር መንገድ እንዲሰጥ የሚሉና ሌሎችም ሃሳቦች በሰነዱ ላይ ተመልክቷል። እነዚህ  ጉዳዮች በጥቅል ሲታዩ የትምህርት ስልጠና ጥራት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። በሌላ በኩል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል። አገራችን “ዕውቀት ሁሉ ከውጭ የሚገባ ነው” ከሚባልበት ዘመን ወጥታ፣ ዛሬ ላይ በራሷ አቅም ትምህርትን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች ሲሉ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌጤ ይናገራሉ። በዚህም በየደረጃው በሚገኙ የዘርፉ መስኮች የቅበላ አቅሟን በማሳደግ ጥራቱን ማረጋገጥ እንደሚገባም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ይህ ፍኖተ ካርታ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ከማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና አለው ሲሉ  የተናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የጥናቱ አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ ናቸው። ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ እንጂ ክፍት ስራ ፈላጊ እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድም ውጤታማ የሚያደርግም እንደሆነ እነደዚሁ። በተጨማሪም የጥናቱ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ጀለሎ ኡመር እንደተናገሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በአንድ በኩል አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን በበለጠ ሁኔታ እንዲከውኑ የሚያደርግ ነው። ፍኖተ ካርታው የትምህርት ጥራትን የሚያጎለብቱ ሰነዶች፣ ከመስክ ጥናትና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ የተገኙ ግብዓቶች የተቀመሩበት ነው። ፍኖተ ካርታው የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የላብራቶሪና የሰርቶ ማሳያ ግብዓቶች በተሟላ መልኩ እንዲኖሩና እነዚህ ካልተሟሉ ከፍተኛ ትምህርት መክፈት አያሰፈልግም የሚል ሃሳብ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የጥናቱ አማካሪ ፕሮፈሰር አክሊሉ ደለሎ ናቸው። በስራ ላይ ያለውን የትምህርት ስልጠና ፖሊሲን የሚያሻሽለው ይህ ፍኖተ ካርታ፤ የሀገሪቱን የሰው ሃይል ፍላጎት መሰረት አድርጎ ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት ዓይነት በፈለጉት ሁኔታ እና በተግባር የታገዘ ትምህርት እንዲያገኙ እንደሚያግዛቸው ከሰነዱ መረዳት ይቻላል። ፍኖተ ካርታው በፍላጎትና በአቅርቦት የተሟላ ትምህርት በማቅረብ ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር ብቁ ሃይል ለማፍራት እገዛ ይኖረዋል። እንዲሁም ቀደም ሲል የነበረውን የትምህርት መዋቅር የሚያሻሽልና ዩኒቨርስቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖራቸው የሚግዝ ነው። ሌላው በፍኖተ ካርታው እንደ መነሻ ሀሳብ የቀረበው ደግሞ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት፣ ከ7ኛ እስከ 8ኛ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሁም ከ9ኛ እስከ 12ኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ተብሎ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ጎን ለጎን የሚሰጥበት መርሃ ግብርን ያካተተ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ስልጠና ሚኒስቴር፣ አጠቃላይ የትምሀርት ስልጠና ሚኒስቴርና  የክህሎትና ስራ ፈጠራ ሚኒስቴር ተብሎ ለሶስት በመክፈል ለውጤታማነት መሰረት የያዘ ነው። በተመሳሳይ ሰነዱ መምህራንን በተለያዩ የማትጊያ ስርዓት ለማበረታታት ቢያንስ ቢያንሰ ከሌሎች ሙያዎች ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን በማድረግ አሁን ያሉ ጥሩ ጅምሮች ተጠናክረዉ ይቀጥሉ፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ የመምህራን ሆስፒታል ማራኪና መምህራንን በጥረታቸዉና ችሎታው ልክ ለይቶ የሚክስ እርከን ማዘጋጀት የሚሉ ነጥቦችም ተካተዋል። በፍኖተ ካርታው ውስጥ የሚታዩ ብዥታዎች እና ፈተናዎቹ በፍኖተ ካርታው የተዘረዘሩት መነሻ ሀሳቦች በትክክል ከተተገበሩ እና ወደ ተግባር ከተለወጡ በአገሪቱ አሁን ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ይፈታል የሚል እምነት ያስይዛል።  ነገር ግን በአጭር ጊዜ የተባሉ ነገሮችንና የተገኙ ክፍተቶችን ማሟላት እንደ አገር ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ከባድ አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው። ከነዚህም መካከል አንደኛ የአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ብቁ የሰው ኃይል ችግር እንደገጠማት ያስረዳል፡፡ መንግሥት የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ የያዙ እንዲሆኑ አልሞ ቢንቀሳቀስም ሙሉ በሙሉ ማዳረስ አልተቻለም፡፡ በሌላ በኩል አዲሱ ፍኖተ ካርታ የአሥራ አንደኛና የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መምህራን የሁለተኛ ዲግሪ እንዲኖራቸው ይደነግጋል፡፡ ይህ አሰራርና አዋጅ ዩኒቨርሲቲዎቹ ያላገኟቸው የሁለተኛ ዲግሪ የያዙ መምህራንን በየ ትምህርት ቤቶች ማካተት በአንድ ሌት የማይሰራ ነገር በመሆኑ የሚከብድ ነገር ይመስላል። ሁለተኛ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል የትምህርት ሽፋን አሁንም በጣም ዝቅተኛ ነው (በተለይ ቅድመ መደበኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት)፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች ተዘርዝረዋል፡፡ ችግሩ ከፍላጎትም ከአቅርቦትም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከቅድመ መደበኛ እስከ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ ግዴታ እንዲሆን ለማድረግ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ አገራዊ አቅም ይጠይቃል፡፡ ከዓለም አቀፍ አገሮች ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆኑት ብቻ የግዴታ ትምህርት ሕግ እንዳላቸው ከዩኒሴፍ የተገኘ መረጃ ያስረዳል። ለምሳሌ  ከአፍሪካ አገራት መካከል ግብፅ፣ ሞሮኮና ዚምባብዌ ብቻ ናቸው ይህንን አስገዳጅ ትምህርት የሚተግብሩት፡፡ በተመሳሳይ ለውውይት በቀረበው በዚህ ሰነድ ላይ በተቀጣጠለው የለውጥ ሂዴት ውስጥ የበለጠ ተግባራዊ ስራዎችን ከኢንዳስትሪ ግብዓት ጋር በማቆራኘት የተያዘውን ዕቅድ ግብ ለመምታት የሚያስችል አይመስልም። ለምሳሌ በሰነዱ ዩኒቨርሲቲዎች በቂና ችግር ፈች የሆነ ምርምር እያደረጉ እንዳልሆነ፣ ምርምር የሚያደርጉ መምህራን ቁጥርም በጣም አናሳ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔ ደግሞ ምክረ ሐሳቡ የማስተማር፣ የጥናት፣ የአገልግሎት ምጥጥን 60፣ 25 እና 15 እንዲሆን ያዛል፡፡ ጥያቄው በ25 በመቶ የሥራ ሰዓት ብቻ የተሠራ ምርምር በቂ ነው ወይ? ምጥጥኑስ እንደየ  መምህራኑ ብቃትና ደረጃ መሆን የለበትም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ያጭራል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ቁም ነገር ደግሞ ጥራት ያለው የምርምር ሥራ ከፍ ያለ ሥልጠናና ልምድ ይጠይቃል፡፡ ራስን ችሎ ሰፋ ያለ የጥናት ፕሮጀክት ለመምራት በሦስተኛ ዲግሪ (ዶክትሬት) ደረጃ በሚሰጥ የምርምር ሥልጠናና ልምድ ማለፍ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያሏት ሦስተኛ ዲግሪ የያዙ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ብዛት 15 በመቶ ብቻ እንደሆነ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከሰሃራ በታች ካሉ እንደ ጋና፣ ኡጋንዳና ኬንያ ያሉ አገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ዓለም በፈጣን ለውጥ ላይ በመሆኗ  በዚህ የለውጥ ሒደት ለመሳተፍና ለመጠቀም፣ ዜጎች ጊዜውን የሚመጥን ዕውቀትና ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር የፖሊሲ ሰነዱ ሥርዓተ ትምህርቱን በተመለከተ ስለሚደረጉት ለውጦች ሲዘረዝር በገጽ 69 ላይ፣ ‹‹በሁሉም ደረጃዎች ሥርዓተ ትምህርቱ ከዕውቀት ወደ ክህሎት ትኩረት እንዲሸጋገር/እንዲለወጥ ማድረግ›› አስፈላጊ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ ይህ መታረቅ ያለበት ክህሎት ከባዶ አይነሳም፣ ከዕውቀት ጥንስስ የሚገኝ ውጤት ነው፡፡ ያለ በቂ ዕውቀት የማሰብ ክህሎት ዕውን አይሆንም፡፡ ያለ ዕውቀት ፈጣሪ፣ ምክንያታዊ ተወዳዳሪና ተሳታፊ ዜጋ መገንባት አይቻልም፡፡ ለሁሉም ዕውቀት አስፈላጊው ግብዓት ነው፡፡ በቴክኖሎጂና በኢኮኖሚያዊ ልማት ግንባር ቀደም የሆኑ አገሮች ሥርዓተ ትምህርታቸው ዕውቀትና ክህሎትን አመዛዝኖ የያዘ ነው፡፡ ለእኛም የሚያስፈልገን ሁለቱን አጣጥሞ የሚሰጥ ሥርዓተ ትምህርት መሆን አለበት፡፡ በአንድ በኩል ‹ግባችን ዕውቀት መር ልማት ነው› እያልን፣ በሌላ በኩል ‹ትምህርታችን ትኩረቱ ከዕውቀት ይልቅ ክህሎት ላይ ይሁን› ማለት ግልጽ ተቃርኖ ይመስላል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ የገጠመው ችግር የፖሊሲ ሐሳብ እጥረት ብቻ አይደለም፡፡  በ1986 ዓ.ም. ችግሮቻችንን ለይተን፣ ግባችንን ተልመን ወደ ሥራ ገባን፡፡ ከ24 ዓመታት በኋላ ችግሮቹ አልተፈቱም፡፡ ስለዚህ በግባችንና በውጤታችን መካከል ያለውን ክፍተት መመርመር አለብን፡፡ እስካሁን ያልተፈቱት የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ ጥራትና አግባብነት ችግሮች አስፈላጊው ፖሊሲ ባለመኖሩ ሳይሆን መንግሥት ራሱ እንዳመነው፣ ”በፖሊሲው መሠረት ባለመፈጸም፣ በየደረጃው በፖሊሲው ላይ ግልጽነት ባለመፍጠራችንና በአግባቡ መተግበር ባለመቻላችን” ነው፡፡ ይህ ለመጪዎች 15 አመታት የሚያገለግል የትምህርት ፍኖተ ካርታ ከስህተት የመማር ዕድል እንዳይዘጋ እውነተኛ፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት እንደ ዋና መርህ ቢቀመጥ፣ የተቀረፀበትን ዓላማ ማሳካት የሚያስችል ፖሊሲን ለማረም ድጋሜ 24 ዓመታትን መጠበቅ እንዳይኖርብን፤ ካረጀ ንስር አሞራነትም እንድናለንና። በአጠቃላይ በጥራት ላይ የተመሰረተው ይህ አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ አገራችን የጀመረችውን ለውጥ የሚያጠናክርና አቅም ያለውን የሰው ሃይል በሁሉም መስኮች ለመፍጠር የሚያስችል ለማድረግ ይረዳ ዘንድ በሰነዱ ውስጥ ያሉትን እነዚህን  ብዥታዎችም ሆኑ ሌሎች አሰራሮችን በመቅረፍና የጋራ መግባባት በመፍጠር ለተግባራዊነቱ ሁሉም ዜጋ ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋፍ ማድረግ ይገባል መልዕክታችን ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም