የክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግርና የብሔር ግጭት በዶክተር አብይ የአመራር ዘመን እንደሚፈታ ተስፋ አለን - ነዋሪዎች

92
ጋምቤላ ግንቦት 12/2010 በጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግርና የብሔር ግጭት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የአመራር ዘመን እንደሚፈታ ተስፋ እንዳላቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ጋር በዛሬው ዕለት በመወያየት ላይ ናቸው። ዶክተር አብይ አህመድ በደምቢዶሎ ከነበራቸው ቆይታ በኋላ ጋምቤላ ገብተው ከህዝብ ጋር ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ። የጋምቤላ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በክልሉ ስላለው የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮች አንስተዋል። አንዳንድ ተወያዮች እንዳነሱት፤ በጋምቤላ የነበረው የመልካም አስተዳደር እጦትና የዜጎችን ስደት የወለደው የብሔር ግጭት በዶክተር አብይ የአመራር ዘመን ይፈታል። የደን መጨፍጨፍና የብሔረሰቦች እኩልነት ማጣትም የክልሉ ዋነኛ ችግር እንደሆነ ከተሳታፊዎች ተነስቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በነዋሪዎቹ እየተነሱ ባሉ ሀሳቦች ላይ ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል። ዛሬን ጨምሮ የሁለት ቀናት ቆይታ በጋምቤላ የሚያደርጉት ዶክተር አብይ ነገ በጋምቤላ ስታዲየም ተገኝተው ለአብዛኛው የጋምቤላ ነዋሪ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሪፖርተራችን ከስፍራው ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም