የድሬዳዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል.... ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል.... ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን
ድሬዳዋ መስከረም 29/2011 የድሬዳዋ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት ከ700 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ተናገሩ፡፡ ላለፉት ዓመታት በመገንባት ላይ ከሚገኘው ፕሮጀክት የቶሚ ሳይት ተጠናቆ የሙከራ የውሃ ስርጭት እያደረገ ቢሆንም በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግርና በልማት ተነሺዎች ምክንያት እንቅፋት እንዳጋጠመው ተጠቁሟል፡፡ የመጠጥ ውሃ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በአስተዳደሩና በዓለም ባንክ በተመደበ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የንፁህ መጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን ፕሮጀክት በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ በድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የተመራውና በቅርቡ የተሾሙት የአስተዳደሩ ካቢኔ አባላትን ያካተተ ቡድን ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ደረጃ ትናንት ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የድሬዳዋ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እንዳስታወቀው በሰኮንድ 496 ሌትር ውሃ የሚያመነጩ 14 ጥልቅ ጉድጓዶች ሥራ ተጠናቆ ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል። ከአንድ እስከ አራት ሺህ ሜትር ኩዩብ ውሃ የሚያጠራቅሙ ጋኖች ተገንብተው መጠናቀቃቸውንም ባለስልጣኑ ገልጿል። ከእዚህ በተጨማሪ የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የቧንቧ ቀበራና የመንገድ ሥራዎች ያለቁ ሲሆን የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራም 60 በመቶ ላይ መድረሱን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡ የባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ሙሴ እንዳሉት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በመገንባት ላይ ከሚገኘው ፕሮጀክት የቶሚ ሳይት በቀን 8 ሰዓት የሙከራ ስርጭት ማድረግ የጀመረ ሲሆን ፕሮጀክቱ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል እና ፕሮጀክቱ በሚከናወንበት ሥፍራ ከአንድ ጋራዥ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ችግር በመፍታት ከሁለት ወራት በኋላ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ ሲገባ 32 ሺህ 140 ሜትር ኩዩብ ተጨማሪ ውሃ በማሰራጨት የከተማውን የውሃ አቅርቦት ከ40 ወደ 90 በመቶ ከፍ በማድረግ የውሃ ችግሩን እንደሚፈታ ጠቁመዋል፡፡ " የመልካ ጀብዱ ቀበሌ ነዋሪዎችን የውሃ ችግር ለመፍታትም በ550 ሚሊዮን ብር አዲስ የውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ለመተግበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል " ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው ህዝብ በጉጉት የሚጠብቀው ፕሮጀክት በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አመራሩና ሠራተኛው እያደረገ ያለው ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ለኤሌክትሪክ አገልግሎት 46 ሚሊዮን ብር ከዓመት በፊት ክፍያ መፈፀሙን አስታውሰው ፕሮጀክቱ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎችም ተገቢው ቦታና ክፍያ ተፈጽሞ እንዲነሱ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ "መፍትሄ ላላገኘው አንድ የጋራዥ ባለቤት ተገቢው ምትክ ቦታ በቅርቡ በመስጠት በሳቢያን አካባቢ የተጠናቀቀው የፕሮጀክቱ አንዱ ክፍል ወደ ሙከራ ስርጭት እንዲገባ ይደረጋል" ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የድሬዳዋ ዲስትሪክት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቅረማርም አለማየሁ ችግሩን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ተቋማቸው ለፕሮጀክቱ መፋጠን በትኩረት እየሰራ ቢሆንም በአካባቢው ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግርና ከውጭ ሀገር የሚገቡ ትራንስፎርመሮች በጊዜ አለመድረስ ስራው መዘግየቱን ተናግረዋል፡፡ በአሁን ወቅት ሁሉም ችግሮች መፍትሄ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸው ቀሪውን ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግና ቀነ ገደቡን ለማስቀመጥ ግን እንደሚቸገሩ አስረድተዋል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አብዛኛው ክፍል በተለይ በአስተዳደሩ ጠረፋማ ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ከፍተኛ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር እንዳለባቸውና አስተዳደሩም ችግሩን ለመፍታት ያከናወናቸውን ተግባራት ኢዜአ ላለፉት ዓመታት ደጋግሞ መዘገቡ ይታወሳል፡፡