የምዕራብ ወለጋ ዞን ከቱሪዝም የማገኘውን ገቢ ለማሳደግ እጥራለሁ አለ

51
ጊምቢ መስከረም 29/2011 በዞኑ የሚገኙትን የቱሪስት መስህቦችን በመንከባከብና የመሠረተ ልማት ተቋማትን በማሟላት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚሰራ የምዕራብ ወለጋ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ሀዋ አብዱ የዓለም ቱሪዝም ቀን በቂልጡ ካራ ወረዳ በተከበረበት ወቅት የዞኑን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች በመንከባከብና ተቋማቱን በማሟላት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል፡፡ በዚህም ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም የሚያሳድጉ ሥራዎች መስህቦቹን  በማስተዋወቅና ተቋማቱን በማሟላት እንደሚያከናውን አስረድተዋል። የቂልጡ ካራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተስፋ መላኩ  በበኩላቸው በወረዳው የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ከዘርፉ መገኘት ያለበት ጥቅም እያስገኙ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማስተባበር በተለይ የመንገድ ሥራዎችን ለማሟላት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ደግሞ ሌሎች  የመሠረተ ልማት ተቋማትን እንዲያሟላላቸው  አስተዳዳሪው ጠይቀዋል፡፡ በዞኑ ለቱሪስት መስህብነት የሚውሉ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች የማስተዋወቅ ሥራ ስለማይከናወን  ፏፏቴውን ጨምሮ ሌሎችን መስህቦችን ጎብኝተው እንደማያውቁ የወረዳው ነዋሪ አቶ ተመስጌን ሙላቱ  ተናግረዋል። መንግሥት የመሠረተ ልማት ተቋማትን ለማሟላት ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብሏል፡፡ ኅብረተሰቡ የተፈጥሮ ደንና የዱር እንስሳትን በመጠበቅና በመንከባከብ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን መሥራት ይገባዋል ያሉት ደግሞ  አቶ ምስጋና ገለታ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ቀን በዞኑ ደረጃ የተከበረው ''የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር ለቱሪዝም ልማት!'' በሚል መሪ ሃሳብ ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም