ቀጥታ፡

ጅግጅጋ ስምንተኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ታስተናግዳለች

ጅግጅጋ  መስከረም 29/2011 በጅግጅጋ ከተማ ለሚከበረው ስምንተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ዝግጅቱ መጀመሩን የከተሞች ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ ሚኒስቴሩ ከሶማሌ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር በመተባበር የበዓል አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በከተማው ተካሂዷል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት  የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ብራሳ እንዳሉት በከተማዋ የሚዘጋጀው ፎረም የክልሉ ባህል ለማስተዋወቅና ከተሞችያላቸውን መልካም ተሞክሮ ይለዋወጡበታል። የሶማሌ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዲፈታህ ሼህ ቢሒ እንዳሉት ፎረሙን ለማስተናገድ ኮሚቴዎች በክልል ደረጃ ተቋቁመው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው። ፎረሙ በከተማዋ ባለፈው ዓመት መጨረሻ የተፈጠረውን መጥፎ ስሟን ለመቀየር እንደ መልካም አጋጣሚ እንደምትጠቀምበትም ገልጸዋል፡፡ በፎረሙ ለሚስተናገደው ኤግዚቢሽን አራት ሄክታር መሬት፣የፓናል ውይይቶች የሚደረግባቸው አዳራሾችና የእንግዶች ማረፊያ ቦታዎች ዝግጅት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል። ፎረሙ ከተሞች ነዋሪዎቻቸውን በማሳተፍ ለአገራዊ እድገት የሚጠበቅባቸው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ፣ በከተሞች የሚታዩ ችግሮች ህዝቡ በራሱ ጥረት እንዲፈታ የተሻለ አስተሳሰቦች የሚቀርቡበት ነው። በተጨማሪም በከተሞች መካከል ጤናማ ውድድር እንዲኖርና የልምድ ልውውጥ ለማካሄድ ዓላማ ያለው ዓመታዊ ዝግጅት መሆኑን በውይይቱ ላይ የቀረበው መሪ ሰነድ ይገልጻል፡፡ በጅግጅጋ ከተማ በሚዘጋጀው ስምንተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከ20 ሺህ በላይ እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሉ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም