ቀጥታ፡

የስፖርት አካዳሚው የግሉ ዘርፍ ትኩርት በማያደርግባቸው የስፖርት አይነቶች ላይ ስልጠና እየሰጠሁ ነው አለ

አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የግሉ ዘርፍ ትኩረት በማያደርጉባቸውና ሀገሪቱ ውጤታማ ልትሆን በምትችልባቸው የስፖርት አይነቶችን ለማሳደግ እሰራለሁ ነው አለ። የውሃ ዋና፣ የዱላ ቅብብል፣ መሰናክል፣ የከፍታ ዝላይ፣ የርዝመት ዝላይና ሌሎች መሰል የአትሌቲክስ ሜዳ ላይ ውድድሮች የግሉ ዘርፍ ብዙም ትኩርት ከማይሰጣቸው የሚመደቡ የስፖርት ዘርፎች ናቸው። ሆኖም ግን እነዚህ ስፖርታዊ ውድድሮች ተገቢውን ትኩረት ቢያገኙ አገሪቱ ውጤታማ ልትሆን የምትችልባቸው መሆናቸውን የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው ለኢዜአ ገልፀዋል። በመሆኑም በእነዚህና ሌሎች መሰል የስፖርት አይነቶች ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሸፈን አካዳሚው የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ የሚሰራ መሆኑን  አስታውቀዋል። አካዳሚው ባለፉት ዓመታት ስልጠና ሲሰጥባቸው የነበሩ የስፖርት አይነቶች እንዳሉ ሆነው በአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍ በሚመደበው የምርኩዝ ዝላይ የስፖርት አይነት ስልጠና መስጠት እንደሚጀምር አስታውቀዋል። ለስልጠናው የሚያግዙ ቁሳቁሶች መገዛታቸውን፤ የስፖርተኞች ምልመላም መካሄዱን ገልጸዋል። ከዚህ ውጭ በሌሎች የሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ስፖርት ተግባራት ከሚባሉት ውስጥ እንደ ጦር ውርወራ፣ የከፍታ ዝላይ፣ የርዝመት ዝላይና ሌሎች የመም ተግባራት ላይም ትኩርት አደርጎ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በዚህ ዓመት በአካዳሚው የሚሰጠውን ስልጠና ለመከታተል 118 የሚሆኑ ስፖርተኞች ተመልምለዋል። በዓመቱ የተያዘው እቅድ 209 ስፖርተኞችን ለመቀበል ቢሆንም በአካዳሚው ምልመላ ፈተናውን ያለፉት ግን 118 ስፖርተኞች ናቸው ብለዋል። አሁን ከተመለመሉት ውጭ በተጨማሪ ስፖርተኞችን የመመልመል ተግባርም በቀጣይ የሚከናወን መሆኑን ተናገረዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ለታዳጊዎቹ ስልጠናውን የሚሰጠው በአዲስ አበባ እና በጥሩነሽ ዲባባ ካምፓሶቹ የአትሌቲክስ ስፖርት፣ ውሃ ዋና፣ የቦክስና፣ ብስክሌትን ጨምሮ በ10 የስፖርት አይነቶች ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ለታዳጊዎች ስልጥና ከመስጠት ባሻገር ችግር ፈቺ  ጥናትና ምርምር ያካሄዳል፤ ለዘረፉ ባለሙያዎም  የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ያዘጋጃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም