በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ህዝባዊ ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ህዝባዊ ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ህዝባዊ ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ። በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚከበረው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይከበራል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች እየተፈጠሩ በመሆናቸው ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓሉ ግጭቶችን ለማስቀረት ሲባል በአደባባይ እንደማይከበር መገለፁም የሚታወስ ነው። ይህንን ተከትሎ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የምክር ቤቱ አባላት፤ በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ህዝባዊ ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ ነው የገለፁት። የምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ እርቅነሽ ዮሃንስ በሰጡት አስተያየት "አሁን ባለው ላይ የግንዛቤ እጥርት ካል ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ወይም ለውጥ እንፈልጋላን ከሆነም ደግሞ ህዝቡ ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚፈልግ ውይይት ተደርጎበት ወደ የተስማማንበት አቅጣጫ እስከ መንሄድ ነው፤ ሆኖም ግን ባንዲራ ህዝቡን ሊያጋጭ ሊያጣላ አይገባም የሚል አቋም አለኝ።" ብለዋል፡፡ "የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ተነጋግረው ለእኛ ይሆናል ብለው ያስቀመጡት ነገር ነው ፤ ምናልባትም የሚቀየሩ ነገሮች ካሉ ህዝቡ በደንብ እስከ ታች ተወያይቶ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሃሳብ ታክሎበት መስተካከል ያለበት ነገር ይስተካከላል።" በማለት የገለጹት የምክር ቤት አባል አቶ ዮሃንስ ካሳሁን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ናት። ሆኖም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እስከ 1890ዎቹ አጋማሽ ድረስ በቀለማትም አንድ ወጥ እንዳልነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ ወጥነት ባለው በተያያዙ አራት ማእዘናት በጥቅም ላይ የዋለው በ1890ዎቹ መጨረሻ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰንደቅ ዓላማ ልዩ ትርጓሜና ስርፀት የተሰጠው ደግሞ በ1898ዓ.ም እንደሆነም እንዲሁ። አሁን በሥራ ላይ እየዋለ ያለው ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴው የልምላሜ፣ ቢጫ የተስፋ፣ ቀይ የመስዋዕትነትና ጀግንነት ምልክት ተደርጐ የሚወሰድ ሲሆን መሃል ላይ ያለው ብሔራዊ አርማ ደግሞ የብሄሮች ብሄረሰቦች ህዝቦችና የሃይማኖቶች እኩልነትና አንድነት የሚያመላክት ነው።