ቀጥታ፡

የአገር ሽማግሌዎች ግጭቶችን በመከላከልና በማረጋጋት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው

ሶዶ መስከረም 29/2011 የአገር ሽማግሌዎች ግጭቶችን በመከላከልና ሲፈጠሩም በማረጋጋት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የጋሞና የኦሮሞ የአገር ሸማግሌዎች አሳሰቡ፡፡ የአገር ሽማግሌዎቹ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዳስረዱት ሽማግሌዎች በአካባቢያቸው የሚያጋጥሙ ግጭቶችን አስቀድሞ በመከላከል፤ካጋጠሙም ሕዝቡን በማረጋጋት ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። የጋሞ አገር ሸማግሌ አቶ ሳድቃ ሳምአ የአገር ሸማግሌዎች አገርን በማረጋጋትና ሰላምን በማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ይናገራሉ። በዚህም ልምዳቸውን ተጠቅመው ግጭቶች እንዳይከሰቱ ይከላከላሉ።ችግሮችን በመፍታትና የተጣሉትንም በማስታረቅ ሚናቸውን  መጫወት እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡ አገር ሽማግሌዎች ግጭቶችን ለመፍታትና ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ይላሉ።የጋሞ አባቶች የፀብ ምልክት በሚያስተውሉበት ወቅት እርምጃ በመውሰድ ግጭቶችን እንደሚከላከሉም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ሽማግሌዎቹ ፀብ ከተፈጠረ በኋላ የአፀፋ እርምጃ እንዳይወሰድ ማድረግ አለባቸው ያሉት አቶ ሳድቃ፣ በጋሞ ባህል የአፀፋ እርምጃ መውሰድ እርግማን ወይም ''ጎሚን'' እንደሚያስከትል ተናግረዋል፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ዜጎች ግጭት ሲፈጠሩ በስሜትና በቁጣ ተገፋፍተው የኃይል እርምጃ ለመውሰድ የሚዘጋጁ ሰዎችን መምከር  ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። በአገሪቱ የተጀመረውን የአንድነትና የአብሮነት ጉዞ ለማስቀጠል የአገር ሸማግሌዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ የሚኖሩ አባቶች ግብረ ግብነትን በማስተማር ወጣቶችን የመገሰፅ፣ የመምከርና ቀኖናዊ መንገድ የማሳየት ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የጋሞ አገር ሸማግሌ አቶ አምለ አልቶ ናቸው፡፡ የአገር ሸማግሌዎች ግጭቶችን ሊፈጠሩ እንደሚችሉ  መረጃ ከደረሳቸው አስቀድመው ለመከላከልና ከጉዳት ለማዳን መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውንን በውይይት የሚያምኑ ዜጎች አድርገው ማሳደግ እንዳለባቸውም የአገር ሽማግሌው ይመክራሉ። መንግሥትም በየአካባቢው ያለው ባህል በማሳደግና በማጎልበት ሰላምን የማረጋገጥ ሚናውን መጫወት እንዳለበት አስረድተዋል።በባህላዊ ሥርዓት ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደለሌበትም በማመልከት፡፡ ከመንግሥት ጎን ቆመን ከሰራን አገሪቱን ከኋላ ቀርነት፣ ከድህነትና ከግጭቶች የምናወጣበት ጊዜ ሩቅ ሳይሆን ቅርብ ነው ብለዋል፡፡ በሽምግልና ሥርዓት ውስጥ አንድነት የሚያጠናክሩ የመሃላ ስርዓቶች በኦሮሞዎችና በጋሞዎች ዘንድ እንደነበሩ ያስታወሱት ደግሞ የጋሞ አካባቢ ነዋሪ አቶ ዳብሮ ዳርጮ ናቸው፡፡ መንግሥት የግጭት አፈታትና አሸመጋገል ባህል ያለውን አገራዊ ፋይዳው በመረዳት የሚጠናከሩበትን መንገድ መፍጠር ይገባዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የኦሮሞ አባገዳዎች ምክር ቤት አባልና የቡራዩ አባገዳ መልካ ኡርሶ በበኩላቸው የአገር ሽማግሌዎችና አባቶች የአገሪቱን  ሰላም፣ እድገትና አንድነት የማይወዱ አካላት ግጭቶች በመፍጠር ላይ  መሆናቸውን ተገንዝቦ መታገል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች በቅርቡ የዓርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች ሊያደርሱ ከነበረው ጉዳት እንዲታቀቡ በማድረግ አድናቆትና ክብር  ማግኘታቸው ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም