የኢትዮጵያ ብሄራዊ ፓርኮችንና ብርቅዬ የዱር እንስሳትን በፎቶ የሚያስተዋውቀው መጽሃፍ ተመረቀ

171
አዲስ አበባ  መስከረም 29/2011 በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሄራዊ ፓርኮችንና ብርቅዬ የዱር እንስሳትን በፎቶ የሚያስተዋውቅ መጽሃፍ "ዋይልድ ላይፍ ኦፍ ኢትዮጵያስ ናሽናል ፓርክ" በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ ትናንት በብሄራዊ ትያትር ለምርቃት በቃ። ባለ 257 ገጽ የሆነው ይህ መጽሃፍ በኢትዮጵያዊው የካሜራ ባለሙያ አዚዝ አህመድ የተዘጋጀ ነው። መጽሃፉ የባሌ፣ የሰሜን ተራሮች፣ የነጭ ሳር፣ የኦሞ፣ የአቢጃታ ሻላ፣ የአዋሽና ሃላይ ደገ የተባሉትን ሰባት ብሄራዊ ፓርኮች ገጽታና በውስጣቸው የያዟቸውን ብርቅዬ እንስሳቶችን የሚያሳይ ነው። ፓርኮችን ቦታው ድረስ ሄደው መጎብኘት ለማይችሉ በፎቶ መልክ ለማስተዋወቅ መጽሐፉ የሚያግዝ ሲሆን የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል። ''እንደዚህ አይነት መጽሃፍ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ሲዘጋጅ የመጀመሪያ ነው'' ተብሏል። የመጽሃፉ አዘጋጅ አዚዝ አህመድ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገረው፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የበለጸገች አገር ብትሆንም ይህንን ሃብት ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ክፍተቶች አሉ። ይህ መጽሃፍ እነዚህን ክፍተቶች በማስተካከል የቱሪዝም ሃብቶችን ለዓለም ለማስተዋወቅና የቱሪስቶች አማራጭ ለማስፋት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግሯል። በኢትዮጵያ ዱር እንስሳትና ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብዙ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም በተገቢው እየተጠቀመችበት አለመሆኗን ገልጸዋል። እነዚህን ቅርሶች ለዓለም በማስተዋወቅ አገሪቱ የቱሪዝም ገቢዋን ለማሳደግ ይህን መሰል መጽሃፍ መዘጋጀቱ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሄራዊ ፓርኮችን መንከባከብና መጠበቅ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኩመራ አሳስበዋል።  ይህን መጽሃፍ በኢትዮጵያ በሚገኙ ብሄራዊ ፓርኮችና ትምህርት ቤቶች አካባቢ ለማሰራጨት መታቀዱንም የመጽሃፉ አዘጋጅ ወጣት አዚዝ አህመድ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም