ቀጥታ፡

ዋልያዎቹ የኬንያ አቻቸውን ነገ በባህርዳር ስታዲየም ያስተናግዳሉ

አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 በ2019 ካሜሮን በምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ በነገው እለት የኬንያ አቻቸውን በባህርዳር ስታዴየም ይገጥማሉ። ሶስተኛ የምድብ ጨዋታቸውን የሚያደረጉት ዋልያዎቹ በጋና ተሸንፈው ሴራሊዮንን ደግሞ አሸንፈው ሶስት ነጥብ አግኝተዋል። ይሁን እንጂ ዋልያዎቹ በጋና 5 ለ0 ሲሸነፉ ሴራሊዮንን 1 ለ0 በማሸነፍ ሶስት ነጥብና አራት የጎል እዳ በመያዝ በጎል ክፍያ ተበልጠው የምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ምድብ የሚገኙት የኢትዮጵያና የኬንያ ብሄራዊ ቡድኖች  ነገ ጨዋታቸውን ሲያደረጉ ጋና እና ሴራሊዮን ከነገ በስቲያ የሚጫወቱ ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ከነገ በስቲያ የሚደረገው የጋና እና ሴራሊዮን ጨዋታ ደግሞ  በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ከሆነ የምድቡ መሪ የሚሆንበት እድል አለው። ዋልያዎቹ የምድባቸውን አራተኛ ጨዋታ  ከአራት ቀን በኋላ  ኬንያ ላይ ያደርጋሉ። በዚህ የማጣሪያ ውድድር እያንዳንዱ ሀገር ስድስት ጨዋታ የሚያከናውን ሲሆን ዋልያዎቹ በህዳር ወር በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ከጋና ጋር ሲጫወቱ በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ደግሞ ከሜዳቸው ውጭ  ከሴራሊዮን ጋር የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም