ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በስሩ ያሉት አራት የስራ ሂደቶች ላልተወሰነ ጊዜ ስራ እንዲያቆሙ አደረገ

አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የአሰራር ክፍተት የተገኘባቸውን የስራ ሂደቶች ከስራ ማስቆሙን አስታወቀ። ድርጅቱ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደጠቀሰው  በትክክል መስራት ያልቻሉና ክፍተት ያሳዩ የስራ ሂደቶች ለጊዜው አገልግሎታቸውን እንዲያቆሙ ተደርገዋል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን እንደገለፁት የድርጅቱ የገበያ ማስፋፋት ልማትና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ልማት ስር የሚገኙ የስራ ሂደቶች  ለጊዜው ስራ አቁመዋል። በዚህም መሰረት የድርጅቱ ዋና ተግባር ከሆኑት መካከል አንዱ በሆነው የገበያ ማስፋፋት ልማት ስር ከሚገኙ የስራ ሂደቶች መካከል ለጊዜው ስራ እንዲያቆሙ የተወሰነባቸው የስራ ሂደቶች አራት መሆናቸውን ተናግረዋል። የቱሪስት አመንጭ ናቸው ተብለው ከሚታሰቡ ሀገሮች ጋር የሚደረጉ የቢዝነስ ለቢዝነስ ስራዎች፣  ከጉዞ ወኪሎች ጋር የሚደረጉ ጉዞዎች ፣አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ሂደቶችና ነባር የፕሮሞሽናል ቁሳቁስ ህትመቶች እንዲሁም  በድርጅቱ በኩል ሰዎችን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እንዲሳተፉ የማድረግ ተግባራት የሚፈጽሙትን ነው ላልተወሰነ ጊዜ ስራ እንዲያቆሙ ያደረገው። በተጨማሪም በቱሪዝም መዳረሻ ልማት በኩል የነባሮችን ግንባታ ማስተካከል በማስፈለጉ አዳዲስ ግንባታዎች እንዲቆሙ መደረጉም ተገልጿል። ድርጅቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በስራ ሂደቶቹ የታዩ ክፍተቶች በመኖራቸው መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሯ  ከድርጅቱ ጋር የሚሰሩ ሌሎች ተቋማት ለጊዜው እንዲታገሱና የማጥራትና የማሻሻል ተግባራት እስኪከናወን ድረስም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ከድርጅቱ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል። ከመስከረም 28 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የስራ ሂደቶቹ ስራ እንዲያቋሙ በመደረጉም ስራዎቹን ከእቅድ ጀምሮ አፈፃፀማቸውንና ከፋይናንስ ጋር በተያያዘም የተጠናከረ የስራ ምዘና እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም