የቲካድ ስብሰባ ኢትዮጵያና ጃፓን መግባባት የፈጠሩበት ሆኖ መጠናቀቁ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የቲካድ ስብሰባ ኢትዮጵያና ጃፓን መግባባት የፈጠሩበት ሆኖ መጠናቀቁ ተገለፀ
ጃፓን መስከረም 29/2011 የኢትዮጵያ ልዑክ ከጃፓን አቻው ጋር በአገራዊና አህጉራዊ ጉዳዮች መግባባት የፈጠረበት በቶክዮ-አፍሪካ የልማት ፈንድ (TICAD) ስብሰባ በስኬት መጠናቀቁ ተገለፀ። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ከጃፓን አቻው ጋር በቀጣይ ዋና የትብብር ዘርፍ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ልዑኩ ከጃፓን አቻው ጋር በአገራዊ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ መክሮ መግባባት ላይ በመድረስ ተሳትፎውን በስኬት አጠናቆ ተመልሷል። ልዑኩ በአፍሪካ አገሮች መካከል ሰፊ የመሰረተ-ልማት ትስስር እንዲፈጠር በማስቻልና ግብርናውን ጨምሮ ደሃ-ተኮር የመንግስት ፕሮጀክቶችን በማዘመንና በመደገፍ ላይ ቲካድ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥና በመጠንም ሆነ በጥራት ይበልጥ እያሳደገ እንዲሄድ ጠይቋል። ሰላም በቀጠናው አገሮች መካከል መተማመን እንዲኖርና የተጀመረው የመሰረተ-ልማት ትስስርና የኢኮኖሚ ውህደት ይበልጥ እንዲፋጠን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ገልጾ በዚህ ረገድ ያለው ትብብርም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጿል። ልዑኩ በኢትዮጵያና ጃፓን መካከል በሁለትዮሽ ትብብር እንዲሁም በቲካድ ማዕቀፍ በካይዘን የጥራት ስራ አመራር ፍልስፍና፣ በግሉ ዘርፍ ልማት፣ በሰው ሃብት ስልጠና፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ሌሎች መስኮች ያለው ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታም መግባባት ላይ ደርሷል። መስከረም 26 እና 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የቲካድ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የተሳተፈው ልዑኩ በቆይታው ከጃፓን አለምዓቀፍ የልማት ትብብር (ጃይካ) ፕሬዚዳንትና ከተለያዩ የጃፓን መንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል። የቲካድ ስብሰባ ዓላማ እ.ኤ.አ በ2016 በተካሄደው ስድስተኛው የቶክዮ-አፍሪካ ልማት ፈንድ የመሪዎች ጉባዔ ወቅት በጃፓን ቃል የተገቡ የትብብር ፕሮግራሞችን አፈጻጸም ለማየትና በቀጣይ የሚኖሩ ትብብሮችን በውይይት በመለየት እ.ኤ.አ በመጪው ኦገስት 2019 በጃፓን ዮኮሃማ ከተማ ለሚካሄደው ሰባተኛው የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳ ለማቅረብ መሆኑንም ተገልጿል። ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2016 በናይሮቢ በተካሄደው 6ኛው የቲካድ ጉባኤ ላይ ተሳታፊ ነበረች፤ በወቅቱ ጃፓን ከ2016-2019 ለአፍሪካ ልማት ከመደበችው 30 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ለመሰረተ-ልማት ከተመደበው 10 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ኢትዮጵያም ተጠቃሚ እንደሆነች ይታወቃል።