ኮሜሳ በንግድ ዘርፍ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል ሥልጠና እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሜሳ በንግድ ዘርፍ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል ሥልጠና እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ኢትዮጵያ ውስጥ ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የሙስና ተግባራትን ለመከላከል ያግዛል በሚል ያዘጋጀው ስልጠና ተጀመረ። ኮሜሳ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የሚሰጠውን ስልጠና ያዘጋጀው ከኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተባባር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ሙስናን ጨምሮ የተለያየ ዓይነት ህገ-ወጥ ተግባር እንደሚፈፀም ይነገራል። ጥራታቸውን ያልጠበቁና ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ፣ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የዋጋ ጭማሪ ማደረግ እና በተመሳሳይ ምርቶች ላይ ወጥ የሆነ ዋጋ መተመን ዋና ዋና ከሚባሉ መካከል መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህም በአገሪቱ ፍትሃዊ ውድድር የሰፈነበት የንግድ መስተጋብር እንዳይፈጠር እንቅፋት ከመሆን ባሻገር በሸማቹና በሀገር ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ላይ ጫና በመፍጠር ላይ ነው። ስልጠናው ታዲያ የኢትዮጵያ ንግድ ማህበረሰብ አባላት በሥራቸው የሚያጋጥማቸውን የሙስና አዝማሚያዎች ለመከላከል የሚያስችል ክህሎት እንደሚሰጣቸው ነው የኮሜሳ የንግድ ምክር ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳንዳራ ዩዌራ የገለፁት። ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ደንቦችንና ሕግጋቶችን መሰረት ያደረገ የሙስና ተግባራት መከላከያ ስልት ለማዘጋጀትም ሥልጠናው ግብአት እንደሚሆን ጠቅሰዋል። የሙስና አደጋ ያለባቸው ተብለው 'ኢንተርናሽናል ትራንስፐረንሲ' በተሰኘውና በዘርፉ ላይ ጥናት በሚያካሄደው ዓለም ዓቀፍ ተቋም በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ደረጃ ከተሰጣቸው 173 የዓለም አገራት መካከል ኢትዮጵያ 107ኛ ደረጃን ይዛለች። ሪፖርቱን በመጋራት የዘርፉ የሙስና ችግርም በጣም አሳሰቢ መሆኑን በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የዋና ፀኃፊው አማካሪ አቶ አዲሱ ተክሌ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ንግዱ ዘርፍ ዘንድ ሁሉም አይነት የሙስና ተግባር እንደሚፈፀምና አንዳንዴም መዋቅራዊ ባህሪ የተላበሱ ሆነው እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል። በመንግሥት መዋቅር ላይ ያለው የአሰራር ወሰብስብነት ችግሩን ያባብሰዋል ያሉት አማካሪው በንግዱ ማህበረሰብ ላይም የሥነ-ምግባር ችግር ይታያል ነው ያሉት። ነጋዴዎች በገንዘብና በሌሎች ጥቅማጥቅም በመደለል ጉዳያቸውን የሚያስፈጽሙበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን አማካሪው አስረድተዋል። ምክር ቤቱ ችግሩን ለማቃለል በተለይም የመንግሥት የአሰራር ሥርዓትን ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲሁም በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት እየታገለ ነው ብለዋል። ለዚህም ከጸረ-ሙስና ተቋምና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት። ሥልጠናው የንግዱ ማህበረሰብ ማጎልበት ካለባቸው አቅሞች መካከል አንዱ በሆነው ሙስና ላይ በማተኩሩ ጥቅሙ የጎላ መሆኑን አማካሪው አረጋግጠዋል። በሥልጠናው በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ምክር ቤት በኩል የተመረጡ ከ50 በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ተሳታፊ ናቸው።