ቀጥታ፡

መንግሥት የዜጎች ደህንነት ለማረጋገጥ ቅድሚያ ሠጥቶ እንዲሰራ ተጠየቀ

አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 መንግሥት የዜጎች ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ቅድሚያ ሠጥቶ መሥራት እንዳለበት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ጠየቀ። ፓርቲው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ፤ በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች በንጽሁን ዜጎች ላይ "በጸረ ሠላም ኃይሎች የሚደርሰው ጥቃትና መፈናቀል መቆም አለበት" ብሏል። ዜጎችም ዘላቂ ሰላም የሚያገኙበትን ደኅንነታቸው የሚያረጋግጥበት እርምጃዎች መንግሥት በአፋጣኝ እንዲወስድም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል። ጎን ለጎንም በሠላማዊ ወገኖቻችን ላይ ጥቃት ያደረሱ ወንጀሎች በሕግ ፊት ቀርበው በሕግ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውም ፓርቲው ጠይቋል። ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትንና ጉዳት የደረሱባቸው ዜጎች መልሰው እንዲቋቋሙና ሠላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለባቸው ፓርቲው አመልክቷል። ለግጭቶች ምክንያት እየሆኑ ያሉት መሠረታዊ ችግሮችም በአግባቡ ተጠንተው ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅላቸውም ፓርቲው በመግለጫው ገልጿል። ፓርቲው ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልና ከሌሎች አካባቢዎች በግጭት ምከንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ችግር እንዳሳሰበው ነው ያስታወቀው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም