የጥጥ ምርታማነትን ለማሳደግ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት እንቅፋት ሆኗል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የጥጥ ምርታማነትን ለማሳደግ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት እንቅፋት ሆኗል ተባለ
አፋር መስከረም 29/2011 በኢትዮጵያ የጥጥ ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ዘርፉ እንዳያድግ እንቅፋት መሆኑ ተገለፀ። ይህንን የገለፁት በአፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ በጥጥ እርሻ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለኃብቶች ናቸው። በአካባቢው በጥጥና ተያያዥ ዘርፎች ምርምር የሚያደርገው የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል በበኩሉ የፋይናንስና የሰው ኃይል እጥረት የሚፈለገውን ዘር ለማቅረብ እክል ፈጥሮብኛል ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዲስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሰሞኑን በአካባቢው የመስክ ጉብኝት አድርገዋል። በዚሁ ወቅትም በተለያዩ ባለኃብቶች የሚካሄዱ የጥጥ እርሻ ልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል። ጉብኝቱ ከተደረገባቸው መካከል የዛሬ አስር ዓመት ገደማ በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ልማት የጀመረው 'አወቀ ፈንቴ የጥጥ እርሻ ልማት" ድርጅት አንዱ ነው። ሥራ አስኪያጁ አቶ አስማሜ ይልማ እንደሚሉት ግን ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ልማቱን እያካሄደ የሚገኘው በ180 ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ነው። ሌላው አብዛኛው መሬት የተሻሻለ የጥጥ ምርት ዝርያ እጥረትን ጨምሮ እየገጠሟቸው ባሉ ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ሳቢያ ጦሙን እያደረ ነው ብለዋል። 'ዲፒ ዘጠና' የተሰኘው የጥጥ ዝርያ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ምርት ስለሚሰጥ እየተጠቀምንበት ነው፤ ይህ ዘር በሄክታር 18 ኩንታል ምርት ይሰጣል ሲሉም ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ጊዜ ተዘርተው ከ60 እስከ 70 ኩንታል በሄክታር የሚያስገኙ የጥጥ ዝርያዎች ከመኖራቸው አኳያ አሁን እየተገኘ ያለው ምርታማነት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም በምርትም ሆነ በጥራት ውጤታማ የሆኑ የጥጥ ዝርያዎች ላይ ምርምር በማድረግ እና ከሌሎች ሀገራት ጭምር በማስመጣት የዘርፉን ልማት ማሳደግ እንደሚገባ ነው አቶ አስማሜ ያሳሰቡት። ሌላው በ200 ሄክታር መሬት በዘርፉ ልማት የተሰማራው 'የአፍሪካ ግሎባል የጥጥ ልማት' ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ተስፋሁን እንደሚሉት ከተሻሻለ ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ባለፈ የኬሚካል፣ የብድር፣ የመስሪያ ቦታ እጥረቶች እንደዚሁም የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግሮች የዘርፉ ማነቆዎች ናቸው። የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ለበርካታ አመታት በጥጥና ሌሎች የግብርና መስኮች ምርምር ሲያደርግ መቆየቱን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ብርሃኑ መገርሳ ገልፀዋል። በዚህም በገዋኔ ወረዳ ምርታማነትንና ጥራት ሊያሳድጉ የሚችሉ የጥጥ ዝርያዎችን በማዳቀል ማግኘት መቻሉን አመልክተዋል። ሆኖም ግን ዝርያዎቹን ለማባዛትና ተጨማሪ ምርምሮችን ለማድረግ የፋይናንስ እጥረት ፈተና እንደሆነባቸው አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የተሻለ ምርት እንደሚሰጡ በተግባር የተረጋገጡ የምርምር ውጤቶች ያለምንም ጥቅም እየባከኑ ነው ብለዋል። በማዕከሉ በጥጥ ምርምሩ የተሰማሩ ባለሙያዎችም የጥናት መስኩን በመቀየር እየለቀቁ በመሆናቸው ዘርፉ የሰው ኃይል እጥረትም እየገጠመው እንደሆነ የምርምር ማእከሉ ዋና ዳይሬክተር አክለዋል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፋይናንስና የሰው ኃይል ጋር በተያያዘ እየገጠመ ላለው ችግር መላ እንዲዘይድ ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጥጥ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ በበኩላቸው በመስክ ጉብኝቱ የታዩ ችግሮችን በጥናት ተለይተው መፍትሔ እንደሚሰጥባቸው አረጋግጠዋል። ባለድርሻ አካላትም በመስክ ጉብኝቱ የታዘቧቸውን ችግሮች ማስተካከል ይችሉ ዘንድ ምክክር ይደረጋል ሲሉም አመልክተዋል። በኢትዮጵያ ባለፈው የምርት ዘመን 100 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ለመሸፈን ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማሳካት የተቻለው ግን ከ60 ሺህ ሄክታር መሬት እንደማይበልጥ ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በተያዘው ዓመትም ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት ከ75 ሺህ እስከ 85 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ይሸፈናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አገሪቱ ከአንድ ዓመት በፊት የጥጥ ልማትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ በዘርፉ ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የ15 ዓመት ብሄራዊ የጥጥ ልማት ስትራቴጂ ይፋ አድርጋ ነበር። በስትራቴጂው መሰረት በአገሪቱ ጥጥ የሚለማበትን መሬት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ 250 ሺህ ሄክታር ለማሳደግ ታስቧል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 19 የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች ያሉ ሲሆን፤ አፋርን ጨምሮ በሰባት ክልሎችም ጥጥ ይመረታል፡፡