መንግስት ለግጭቶችና ለዜጎች መፈናቀል አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል - ተፎካካሪ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለግጭቶችና ለዜጎች መፈናቀል አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል - ተፎካካሪ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ መስከረም 29/2011 መንግስት በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን ማስቆምና ለዜጎች መፈናቀልም አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት እንዳለበት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተናገሩ። ትናንት የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽ ምክር ቤቶች የ2011 የስራ ዘመን መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ በታዛቢነት የታደሙት የፓርቲዎቹ ተወካዮች የአገሪቷ የሰላም ሁኔታ አሳሳቢ ሆኗል ሲሉም ነው ለኢዜአ የገለጹት። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ መንግስት በዓመቱ ለማከናወን ካቀዳቸው ተግባራት መካከል ለዜጎች መፈናቀል ቅድሚያ ትኩረትና መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ይላሉ። የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ትናንት በምክር ቤቱ መክፈቻ ላይ ባስቀመጡት አቅጣጫ ስለ ዜጎች መፈናቀል አጽንኦት እንዳልሰጡ በመጥቀስ። ዜጎች በአገራቸው ዕጣ ፈንታ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በመንግስት ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች በይቅርታ መፈታታቸውና በውጭ አገር የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገራቸው እንዲመጡ መደረጉ ይጠቀሳሉ። ለዚህ ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምህረት አዋጁን ማጽደቁ ጉልህ ሚና ነበረው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር መንግስት ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በሰላማዊ መንገድ ተደራድሮ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል። ይሁንና ሰላምና መረጋጋት ባልሰፈነበት አገር የገዥውም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫና የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማይታሰብ ነው ይላሉ። ፕሬዚዳንቱ በየዓመቱ የሚሰጡት አቅጣጫ ተግባራዊ ሲሆን አይስተዋልም የሚሉት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ ናቸው። በዚህም ምክንያት በየጊዜው ግጭቶች እየተባባሱ ይገኛሉ። ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘመናት በመልካምም ሆነ በፈታኝ የታሪክ አጋጣሚዎች በአብሮነትና በመቻቻል ሲኖር የነበረው የአገሪቷ ህዝቦች እሴት እየተሸረሸረ መምጣቱን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ መንግስት በአገሪቷ ዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። ፕሬዚዳንቱ በምክር ቤቶቹ የስራ ዘመን መክፈቻ ንግግራቸው የመንግስትን የ2011 በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችም አመላክተዋል።