ግምቱ ከአራት ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የኮንትሮባንድ እቃ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
ግምቱ ከአራት ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የኮንትሮባንድ እቃ ተያዘ
አዳማ መከስከረም 28/2011 ግምቱ ከአራት ሚሊዮን ብር የሚበልጥ መድኃኒትና ልባሽ ጨርቅ በኮንትሮባንድ መልክ ወደ ሃገር ውስጥ ሊገባ ሲል መያዙን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን የሚሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አሊ አብደላ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በሶስት ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ሊገባ ሲል ገዳማይቱ ኬላ ላይ የተያዘው እቃ መነሻው ከሶማሌላንድ ነው። የተያዘው መድኃኒት ግምቱ ወደ 2 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሲሆን 260 ኩንታል የሚመዝነው ልባሽ ጨርቅ ደግሞ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ግምት እንዳለው ተናግረዋል። ንብረቶቹን ሲያጓጉዙ የነበሩት ሶስቱም አሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን ገልጸው ለሰው ጤና አደገኛ የሆኑት እነዚህ እቃዎችም እንዲወገዱ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። እቃውን ሲያጓጉዙ ከነበሩት ሶስቱ ተሽከርካሪዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሰሌዳ ያለው ሲሆን ሁለቱ የሶማሌላንድ መሆናቸውንም አመልክተዋል።