ቀጥታ፡

በረቂቅ የትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ ባለሙያዎች የሚሰጡትን ገንቢ ሀሳብ ወደተግባር መቀየር እንደሚገባ ተገለጸ

ሚዛን መስከረም 28/2011 በረቂቅ የትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ  ባለሙያዎች የሚሰጡትን ገምቢ ሀሳብ አሰባስቦ ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ የቤንች ማጂ ዞን ትምህርት መምሪያ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ረቂቅ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በረቂቅ ፍኖተ ካርታው ላይ በባለሙያዎች የሚቀርቡ ገምቢ ሀሳቦችን መንግስት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ከሚዛን ትምህርት በሬዲዮ የመጡት አቶ ንጉሤ ባዩ እንዳሉት የትምህርት ረቂቅ ፍኖተ ካርታው በሚመለከታቸው አካላት እንዲገመገም መደረጉ ጠቃሚ ግብዓት ለማግኘት ይረዳል፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም በባለሙያዎች የሚቀርቡ ሃሳቦችን በግብአትነት በመጠቀም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ''የሚፈለገውን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል'' ብለዋል፡፡ አቶ ንጉሤ አክለውም ውጤታማ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት እንዲቻል የመምህራን ምልመላና ሥልጠና ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ የትምህርት ባለሙያ የሆኑት አቶ አዲሱ አለማየሁ በበኩላቸው የትምህርት ዘርፍ የአመራር ሂደት ከፖለቲካ ነጻ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ተቋማትም አመራርና አደረጃጀትን ጠንቅቀው በሚያውቁ የዘርፉ ሙያተኞች ሊመሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የትምህርት ተቋማትን አስፈላጊ በሆነ ግብዓት ማሟላት እንደሚገባ የጠቆሙት ደግሞ መምህር ብርሀኑ ተሰማ ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቶችን በቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራና ሌሎችም አስፈላጊ በሆኑ ግብዓቶች በማደራጀት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም