ኢትዮጵያ የነጻ ገበያ ስርዓትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደምታደርግ አስታወቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የነጻ ገበያ ስርዓትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደምታደርግ አስታወቀች
አዲስ አበባ መስከረም 28/2011 የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ማረጋጋጥ እንዲቻለው የነጻ ገበያ ሕግጋትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ይፋ አደረጉ። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ይህንን ይፋ ያደረጉት ዛሬ በተከፈተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴራሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የተያዘው ዓመትን ዋና ዋና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ባመለከቱበት በዚሁ ንግግራቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት በተፈጠረው አለመረጋጋትና በአየር ንብረት ለውጥ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ አገራዊው የምጣኔ ኃብት እድገት ማሽቆልቆል ታይቶበታል ብለዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሸቀጦች ላይ የታየው የዋጋ መቀነስም በምጣኔ ኃብቱ ላይ አሉታዊ ጫና ማስደሩን ጠቅሰው ለዚህም የምጣኔ ኃብት ማገገሚያ ፖሊሲ መቀየስ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። በመሆኑም በተያዘው ዓመት የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት በፈጣን ደረጃ ለማሳደግ፤ መንግሥት የነጻ ገበያ ሕግጋትን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ትኩረት አድርጎ ይሰራል ነው ያሉት። ጎን ለጎንም የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ነጻ የገበያ ሥርዓትን ለመገንባትና የተረጋጋ የማይክሮ ኢኮኖሚ እድገትን ቀጣይነት ለማረጋጋጥ ተስማሚ ሁኔታ ለመፈጠርም አጽንዖት ይሰጣል ብለዋል። በዓለም አቀፍ የምጣኔ ኃብት ትስስር አገሪቱ ያላትን ቦታ ለማሻሻል፣ ፍትኃዊ ወድድር፣ እኩልነትና ግልጽነት ያለውን አሰራር በእያንዳንዱ አካባቢ ለማረጋገጥ መንግሥት ዝግጁ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል። የገንዘብ፣ የፊሲካልና ሌሎች ተያያዥ ፖሊሲዎችን በማጣመር የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋትና የምጣኔ ኃብት ሚዛኑን ለማስጠበቅ መንግሥት ትኩረት እንደሚያደርግም አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ እንዳሉት በአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታ ላይ ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጦችን ለማምጣት፤ በፈጠራና በቴክኖሊጂ ላይ የተመሰረተ የእድገት ሞዴል ገቢራዊ ይደረጋል። የመንግሥት ገቢና ወጪ አሰራር ሕግን መሰረት ያደረገ እንዲሆንና የታክስ ጉድለትን በበቂ ሁኔታ ለመከላከል ወጪ ለሚቀንሱ ተግባራት ትኩረት ይሰጣል ሲሉም አመልክተዋል። የመንግሥት ወጪና ገቢ አወቃቀርን በማሰተካከል ለልማት የሚውለው የኢንቨስትመንት መጠን ከፍ እንዲል፤ አገራቱ በብድር የምታገኘውን ገንዘብ በአግባቡ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ለማስቻል ተገቢው ክትትል እንደሚደረግም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። የአገሪቱ የብድር ጣራ በምጣኔ ኃብቱ ከተቀመጠለት ጣሪያ እንዳያልፍ ይደረጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በመንግሥት ዋስትና የሚሰጡ ብድሮች ቀስ በቀስ እንዲቀንሱ ይደረጋል ነው ያሉት። የኢንሹራንስ ተቋማትን አፈጻጸም ቀልጣፋ ለማድረግ፣ የአበዳሪ ተቋማት የተበላሹ ብድሮችን ለማሻሻልና የባንክ ሥርዓት ደህንነትን ለመጠበቅ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የባንክ ሥርዓት ለመተግበር የሚያስችል ቁመና እንዲኖራቸው እንደሚሰራም ጠቅሰዋል። በቅርቡም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ አገሪቱን ለማሰለፍ የሚያስችል የንግድ ሥርዓት መተግበርም ቅድሚያ ይሰጠዋል ብለዋል። በረጅም ርቀት አህጉራዊ ውህደትን ታሳቢ ያደረገ ቀጠናዊ የምጣኔ ኃብት ውህደትን ለመመስረት መንግሥት ወጥና የተቀናጀ የንግድ ፖሊሲና ድርድር በማካሄድ ቀዳሚ ሚና እንደሚኖረውም አክለዋል። የድንበር አከባቢ የንግድ ሁኔታን በሕግ መሰረት ለማሳለጥ ትኩረት ይደረጋል፤ ይህም በቀጠናው እየተገኘ ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማደረግ ይግዛል ብለዋል። ለዚህም ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ ) ሥራውን በተጠናከረ መልኩ እንዲፈጽም መንግሥት የመሪነት ሚናውን እንደሚወጣ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ አረጋግጠዋል። በአፍሪካ ደረጃም የአቡጃን ስምምነት መሰረት በማድረግ አህጉር አቀፍ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረትና ተሳትፎ ኢትዮጵያ በንቃት ትቀጥላለች ብለዋል።