ቀጥታ፡

የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የህግ ማሻሻዎች ይደረጋሉ-ፕሬዚዳንት ሙላቱ

አዲስ አበባ መስከረም 28/2011 የግሉን ዘርፍ በኢኮኖሚ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሕግ ማሻሻዎች እንደሚደረጉ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾሞ አስታወቁ። ፕሬዝዳንቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት የ2011 ዓ.ም የሥራ ዘመን በንግግር ከፍተዋል። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ እንዳሉት፤የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ የሚኖረውን ተሳትፎ ለማሳደግና የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለመሻሻል የተለያዩ ፖሊሲ፣ የሕግና የአስተዳደር ማሻሻያ እርምጃዎች ይወሰዳሉ። ''ከዚህ ባለፈም በመስኩ የሚታየውን የገንዘብ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ የመንግሥት    የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማሳከት የኢንዱስትሪ ፓርክ ስትራቴጂ በአግሮ እንዱስትሪ ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚቀጥል አመልክተዋል። ሰፊና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር የመንግሥት ትልቁ አጀንዳ መሆኑን ገልጸው የስራ ዕድል ፈጠራው አስተማማኝ የሚሆነው የግሉ ዘርፍ ሲስፋፋና ሲጠናከር በመሆኑ መንግሥት የግሉ ዘርፍ ያለበትን ዋናዋና ችግሮች በመለየት ተገቢውን የማሻሻያ እርምጃ ይወስደል፤ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢንም በመፍጠር በአጋርነት ይሰራል በማለት አረጋግጠዋል። ይህንንም መነሻ በማድረግ የግል ዘርፉ ከመንግሥት ልክ ያለፈ ቁጥጥር የህግ፣የአሰራርና ማነቆ እንዳይሸበብ ለማድረግና ዘመናዊ የንግድ እንቅስቃሴን ለማስፈን የሚያግዙ የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚተገበሩ ነው ያመለከቱት። ለአብነትም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሲተገበር የቆየውን የኢትዮጵያ የንግድ ሕግን የማሻሻል ተግባር በበጀት ዓመቱ ተጠናቆ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ እንደሚደረግም ነው ፕሬዝዳንቱ ይፋ ያደረጉት። ከዚህ ባለፈም የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያግዙ አዲስ የኢቨስትመንት ሕግ ዘመናዊ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ እንደሚጠናቀቁ የተናገሩት ዶክተር ሙላቱ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አሰራርን  በቴክኖሎጂ የተጋዘ በማድረግ ቀላል፣ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ የተጀመረውን የሪፎርም ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በተመሳሳይም የጉምሩክ ስርዓቱን ለማዘመንም ርብርብ እንደሚደረግ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ በተለይም የጉምሩክ ስርዓትን ለመፈጸም የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ የአንድ መስኮት አገልግሎት በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል ብለዋል። የውጭና አገር ውስጥ ባለሃብቶች በጥራት መልምሎ ወደ ስራ እንዲገቡ ከማድረግና ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን የሰው ኃይል ለማዘጋጀት ጎን ለጎን በመንግሥት ተይዘው የነበሩ የልማት ድርጅቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለባለሃብቶች በማዘዋወርና መንግሥትም በገበያው የሚኖረውን ድርሻ በመቀነስ  የግል ዘርፉን ተሳትፎ በማሳደግ የኢኮኖሚ እደገቱን ዘላቂ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል። ቅድሚያ ከተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተጨማሪም መሬትን በባለቤትነት በካፒታል ድርሻ በመያዝ በተመረጡ ከተሞች ትላቅ የጋራ ልማት ኢንቨስትመንቶች እንዲካሄዱ በማድረግ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ለቴክኖሎጂ ሽግግርም ሆነ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ይደረጋል። አገሪቷ የገጠማትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል ከሚሰሩ ስራዎች የኢኮኖሚ ሪፎርሞች በተጨማሪ ኢክስፖርትን ለማስፋፋት  በመስኩ የሚታዩ ችግሮችን በጥናት በመለየት ተገቢው የማሻሻያ እርምጃ እንደሚወሰደም ዶክተር ሙላቱ ጠቁመዋል። ጎልቶ የሚታየውን የሎጂስቲክ ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ውጤታማ አለመሆን ችግር ለመቅረፍ እንደሚሰራም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም