ከፍተኛ አመራሩ ህዝቡ የሚጠብቀውን ለውጥ ለማምጣት በትጋት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበት ነዋሪዎች አስገነዘቡ - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ አመራሩ ህዝቡ የሚጠብቀውን ለውጥ ለማምጣት በትጋት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበት ነዋሪዎች አስገነዘቡ
ሽሬ እንዳሥላሴ መስከረም 28/2011 በኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የተመረጠው ከፍተኛ አመራር ህዝቡ የሚጠብቀውን ለውጥ ለማምጣት በትጋት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበት የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ነዋሪዎች አሳሰቡ። ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት ተመራጮቹ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል በብቃት፣ በቅንነት፣ በፍትሃዊነትና በዘላቂነት ለማስቀጠል መሥራት ይገባቸዋል። የወልቃይት ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ገነት ተክሉ አዲሱ አመራር በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉት ግጭቶች እንዲቆሙና በሴቶችና ህፃናት እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ማረም ይጠበቅበታል ብለዋል። ለዚህም በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሞትና ስቃይን ለመከላከል በጥፋት ተልዕኮ የተሰማሩትን አካላትና ተባባሪዎቻቸው ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት ማስከበር ዋናኛ ተግባሩ መሆን አለበት ይላሉ። ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሓጎስ ሀብቱ የመልካም አስተዳደር ጉድለትና ሙስና ለአገሪቱ እድገት እንቅፋት በሚሆንበት ደረጃ ላይ ስለሚገኝ አመራሩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። የፀገዴ ወረዳ ነዋሪው አቶ ጥላሁን ክፍሌ በጉባዔው የሕገ መንግሥት የበላይነትን በማረጋገጥና የብሔር/ብሔረሰቦች አንድነት ባጠናከረ መልኩ በአገራቸው ቀጣይ እድገት ላይ መወሰናቸው ብሩህ ተስፋን አመላካች ሆኖ አግኝቼዋለሁ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። መምህርት መብራት ተክሌ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ጉባዔው የሴቶች ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት መሆኑን አመልክተው፣ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ በአገራቸው ሰርተውና ኮርተው ሃብት የሚያፈሩባቸው ውሳኔዎች የተላለፉበት ነው ብለዋል። “የኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ እህት ድርጅቶች በአንድ አቋም ፀንተው ለአገሪቱ አድነት በቁርጠኝነት ለመታገል ቃል ገብተው የወጡበት በመሆኑ ወሰን የሌለው ደስታ ተሰምቶኛል” ያሉት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ አምሳሉ አያሌው ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)11ኛ ደርጅታዊ ጉባዔውን ባለፈው ሳምንት በሐዋሳ ከተማ ማካሄዱ ይታወሳል።