የካማሽ ግጭት አጣሪ ቡድን በመንገድ መዘጋት ሥራ አልጀመረም - ኢዜአ አማርኛ
የካማሽ ግጭት አጣሪ ቡድን በመንገድ መዘጋት ሥራ አልጀመረም
አሶሳ 28/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን የተከሰተውን ግጭት የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን ቢቋቋምም፤ መንገዶች በመዘጋታቸው ሥራ መጀመር እንዳልቻለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ፡፡ የኮሚሽኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ ኃላፊ ኮሚሽነር ዶክተር አትክልቲ ገብረ ህይወት ዛሬ እንደገለጹት ቅርንጫፉ በካማሽ ዞን የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን አቋቁሟል፡፡ ይሁንና አካባቢው ሙሉ በሙሉ ባለመረጋጋቱ ቡድኑ ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሶ ምርመራውን ማካሄድ አልቻለም ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የምርመራ ሥራውን በአፋጣኝ በጥቅምት ወር እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡ በአሶሳና አካባቢው የተከሰተው ግጭት ምርመራ መጠናቀቁን ያወሱት ኃላፊው ፣ ውጤቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡ በያዝነው ወር አጋማሽ በክልሉ የካማሽ ዞን አስተዳደር አራት አመራሮች መገደላቸውን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ሞተዋል ፤ ከቤትና ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ አጎራባች አካባቢዎች ገብተዋል።