በኦሮሚያ የመንግስት መስሪያቤቶች በአዲስ መልክ ተደራጁ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ የመንግስት መስሪያቤቶች በአዲስ መልክ ተደራጁ
አዳማ መስከረም 28/2011 በኦሮሚያ ክልል ሁሉን አቀፍ የህዝብ ፍላጎት በተሟላ መልኩ ለመመለስ የመንግስት መስሪያቤቶች በአዲስ መልክ እንዲደራጁ መደረጉን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ። የጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ ዓመት አምስተኛ የሥራ ዘመን ሦስተኛ አስቸኳይ ጉባኤ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። ፕሬዚዳንቱ በእዚህ ውቅት እንዳሉት የተቋማት አሰራርን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በክልሉ መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ማጣጠም ያስፈልጋል። " ከአደረጃጀት ጀምሮ የተቋማቱን አሰራርና የህግ ማዕቀፎዕችን በአግባቡ መፈተሽና መከለስ ካልተቻለ የህዝቡን የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ በሚፈለገው ፍጥነት መመለስ አንችልም " ብለዋል። የህዝቡ ጥያቄዎች በየጊዜው እየጨመረ መሆኑንና የገለጹት አቶ ለማ ጥያቄዎቹን በአግባቡ ለመመለስ በክልሉ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በአዲስ መልክ እንዲደራጁ መደረጉን አስረድተዋል። በአደረጃጀቱ ግብርና በተለይ የሰብል፣ የቡናና እና የመስኖ ልማት ሥራዎች ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው መሆናቸውን ጠቁመው ተቋማቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ማሳካት በሚችሉበት መልኩ እንዲደራጁ መደረጉን ተናግረዋል። እንደፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ ውጤታማ የሆነ የመስሪያ ቤቶች አደረጃጀት ለመዘርጋት የክልሉ መንግስት ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ ጥናት አካሂዷል። በአዲሱ አደረጃጃትም 17 ተቋማት በቢሮ ደረጃ የተዋቀሩ ሲሆን ሌሎች ስምንት ተቋማትም በባለስልጣናት፣ በኮሚሽን፣ በኤጀንሲና በኢንስቲቲዩሽን ደረጃ እንዲዋቀሩ መደረጉን ነው የገለጹት። በቢሮ ደረጃ የነበሩት የእንስሳትና አሣ ሃብት ልማት ቢሮ እንዲሁም የበያ ልማት በኤጀንሲ ደረጃ እንዲደራጁ የተደረጉ ሲሆን የማዕድን ልማት ዘርፍ እራሱን ችሎ በባለስልጣን ደረጃ መደራጀቱን አቶ ለማ ተናግረዋል። የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የነበረው በኮሚሽን ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን የወጣቶች ዘርፍ ከሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ጋር ሆኖ እንዲደራጅ መደረጉንም አመልክተዋል። የመንገዶች፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች፣ የአካባቢ ጥበቃ ደንና አየር ንብረት ለውጥ፣ የኮንስትራክሽን ባለስልጣን መስሪያ ቤቶችና የኢኮኖሚ ልማትና ዕቅድ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተጠሪነታቸው ለክልሉ ፕሬዚዳንት እንዲሆን ተደርጓል። በተመሳሳይ ተጠሪነታቸው ለከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ የሆኑት የትራንስፖርት ባለስልጣን፣ የመንግስት ህንፃዎች አስተዳደር ድርጅትና የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት መሆናቸው በመድረኩ ላይ ተገልጿል። የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ አርብቶ አደር ልማት ኮሚሽን፣ የሕብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ፣ የእንስሳት ሃብት ልማት፣ የገበያ ልማትና የግብርና ግብአት አቅርቦት ባለስልጣን እንዲሁም የግብርና ምርምር ማዕከል ተጠሪነታቸው ለክልሉ ግብርና ቢሮ ሆነው ተደራጅተዋል። የጨፌው አባላት በበኩላቸው የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን በሚፈለገው መልኩ ለመመለስ ተቋማቱ በአዲስ መልክ መደራጀታቸው አግባብ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም የተሻሻለው የተቋማት አደረጃጀት ያለውን ውስን ሀብትና የሰው ኃይል አቀናጅቶ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን የጉባኤው ተሳታፊዎች አስታውቀዋል። ጉባኤው የክልሉን የሥራ አስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅና የክልሉን ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ለማደራጀት የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ አጽድቋል ።