ቀጥታ፡

ንቅናቄው በሰላማዊ መንገድ የጀመረውን ትግል እንደሚያጠናክር አመራሮቹ ገለጹ

ባህር ዳር መስከረም 27/2011 ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሂደት መጎልበት በሰላማዊ መንገድ የጀመረውን ትግል እንደሚያጠናክር የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮች ገለጹ። ለአመራሮቹ ዛሬ በደብረብርሃን ከተማ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ስታዲዬም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ንቅናቄው ለህግ የበላይነት መስፈንና ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምና መብት መከበር የሚያካሂደውን ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል። በአገሪቱ የተፈጠረዉን ምቹ ሁኔታም በመጠቀም ለአማራው ህዝብ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ወግ፣ባህልና ማንነት ተከብሮ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶች እንዲዳብሩ ይሰራል ብለዋል፡፡ ዴሞክራሲው  እንዲሰፋና የኅብረተሰቡ እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መንግሥት ጋር በቅንጅት ለመሥራት መዘጋጀታቸውንም ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ለህግ የበላይነት መስፈንና ሌብነትን በመታገል የተጀመረዉ ለውጥ በጥቅመኞች እንዳይቀለበስ ህዝቡ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅ ሊቀመንበሩ አሳስበዋል። ኢትዮጵያዊ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር የመኖር፣የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብቱ ተጠብቆ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎችም እኩል ተሳታፊ እንዲሆን ከመንግሥት ጋር እንሰራለን ብለዋል፡፡ ወጣቱ ጥቅማቸው የተነካባቸዉ ግለሰቦች ብሄርንና ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው በሚያስነሱት ሁከትና ብጥብጥ  መጠቀሚያ መሆን እንደማይገባውም አስገንዝበዋል። በአገሪቱ ነጻነት እንዲሰፍንና ድህነትን ለመዋጋት ተግቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ  የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ነዕማን ዘለቀ በበኩላቸዉ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ባህል፤አንድነትና አብሮነትን በማጎልበት ማንነታችንን ለመሸራረፍ የሚያስቡ ግለሰቦችን መታገል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ምክንያታዊ በመሆን ለአንድነትና ለህዝቡ ተጠቃሚነት በመሞገት ወደ ልዩነት በሚያመሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶና ተቻችሎ በፍቅር የመኖር ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ማጎልበትም ወሳኝ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ በማስቀጠልና ቀጣዩን ምርጫ ፍትሃዊ፣ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የራሳቸዉን ድርሻ እንደሚወጡም ገልፀዋል፡፡ የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ተወካይ አቶ ደስታ አንዳርጌ በበኩላቸዉ በህዝብ ከፍተኛ ትግል የመጣዉ ለውጥ በጥቅመኞች እንዳይደናቀፍ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአንድነትና ለሰላም መረጋገጥ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ለአመራሮች በተደረገዉ አቀባበል የከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች፣የአገር ሽማግሌዎች፣ታዋቂ ግለሰቦች፣የሃይማኖት አባቶችና እንግዶች ታድመውበታል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም