የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተተገበረው ፓኬጅ የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተተገበረው ፓኬጅ የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም
አዲስ አበባ መስከረም 27/2011 የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከ10 ዓመት በላይ የተተገበረው ፓኬጅ የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ። ፌዴሬሽኑ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደረጉ የተለያዩ ፓኬጆች እያዘጋጀ ወደ ትግበራ የሚያመጣ ቢሆንም ተገቢ የሆነ የክትትልና ድጋፍ አሰራር ባለመዘርጋቱ ፓኬጆቹ ውጤት አልባ እንዲሆኑ ማድረጉንም ተጠቁሟል። ከ10 ዓመት በፊት ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የተተገበረው ፓኬጅ ያመጣውን ውጤት በተመለከተ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ተደርጓል። የሴቶች ስትራቴጅያዊ ልማት ማዕከል መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ገነት ዘውዴ ጥናቱ ይፋ በሆነበት ወቅት እንደገጹት፤ በፓኬጁ መተግበር ሴቶች የመቆጠብ ባህላቸውን ማዳበር አስችሏቸዋል። የቁጠባ ባህሉ ያደገ ቢሆንም የተቆጠበውን ገንዘብ ዘላቂ የኑሮ ለውጥና ማሻሻያ የሚሆን ልማት ላይ የማዋል ችግር መኖሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ የሚያመላክት እንደሆነ ጠቁመዋል። ፓኬጁን በመተግበር ረገድ ሰፊ ክፍተት እየፈጠረ ያለው የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው መስራት አለመቻላቸው እንደሆነም ገልጸዋል። በመሆኑም ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግና ለማብቃት የሚስተዋሉትን ችግሮች በጋራ ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊሰሩበት እንደሚገባም ዶክተር ገነት አስገንዝበዋል። የአዲስ አበባ ሴቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ታዘዝ በበኩላቸው በአራት ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ላይ ተካሂዶ የቀረበው የዳሰሳ ጥናት የሴቶችን ችግር ለመፍታት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። ጥናቱ በቀጣይ መንግስት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰራውን ስራ ለመለየት የሚያግዝ ግብዓት የተገኘበት እንደሆነ ገልጸዋል። የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስመላሽ በዛብህ ጥናቱ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎችን የሚያከናውኑ ተቋማት በጋራ አቅደው መስራት እንዳለባቸው መጠቆሙን ተናግረዋል። በየወቅቱ በሚካሄዱ የምክክር መድረኮች ላይ የተከናወኑ ተግባራትና የቀሩ ስራዎችን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የሴቶችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል ስልጠና ለመስጠት ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል። ጥናቱ ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥና ዘላቂ የሆነ አካታች ልማት ለመፍጠር ታልሞ የተደረገ ሲሆን የሚተገበሩ ፓኬጆች ጠንካራ የሆነ ክትትልና ድጋፍ የሚጠይቁ መሆናቸውን አሳይቷል። ጥናቱ በቀጣይም የተቀሩት ሌሎች ክልሎች ላይም እየተካሄደ ሲሆን ሁሉን ያቀፈና ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደረገው ፓኬጅ ተጠናክሮ እንደሚሰራበትም ተገልጿል።