ጉባዔው ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች በአገሪቱ ሠላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዙ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ጉባዔው ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች በአገሪቱ ሠላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዙ ነዋሪዎች ገለጹ
ድሬዳዋ መስከረም 27/2011 ኢህአዴግ በ11ኛው መደበኛ ጉባዔ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች በአገሪቱ ሠላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዙ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ውሳኔዎቹ በአገሪቱ ሰላምን ለማስፈንና ልማቱን ለማፋጠን የተያዘውን እንቅስቃሴ ወደፊት እንደሚያራምዱም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አስታውቀዋል። ጉባዔው ኢህአዴግ ልዩነቶቹን በሰከነ መንፈስ ተወያይቶ የጋራ አቋም እንደሚይዝ ያስመሰከረበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሣቢያን አካባቢ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዓይናለም ደምሴ እንዳሉት ውሳኔዎቹ በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠልና የህግ የበላይነት ለማስከበር ያስችላሉ፡፡ አቶ ዩሱፍ መሐመድ የተባሉ ገንደቆሬ ሰፈር ነዋሪ በበኩላቸው ውሳኔዎቹ አሁን በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታየውን በሰላም ወጥቶ የመግባት ችግሮች እንደሚፈቱ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል፡፡ አቶ ረመዳን አብዱረህማን የተባሉ ሌላው የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው የለውጡ አራማጆች የሆኑት መሪዎች በጉባዔው መመረጣቸው የለውጥ ጉዞውን ለማስቀጠል ያግዛል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የወጣቶች የሥራ እጥነት ችግሮቻቸው ትርጉም ባለው መንገድ እንዲፈታላቸው ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የጠቆመው ደግሞ ወጣት ሰለሞን ዓለሙ ነው። "አንድ ቀን መጥተው እንደሚያወያዩን በተስፋ እየጠበቅን ነው፤ እሳቸው በመደመር መንፈስ የጀመሩትን የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ አስፈላጊውን ሁሉ አደርጋለሁ'' ብሏል፡፡ ወጣት አቡበከር ሙሳ በበኩሉ ወጣቱ በሰከነ መንፈስ አርቆ በማስተዋል የአገሩን ሰላምና ልማት መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ''ተደራጅተን የአካባቢያችንን ሰላም እየጠበቅን ነው። ከእኛ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ ነን'' ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል። ወጣት ሙስተሪያ አህመድ በበኩሏ መንግሥት በየደረጃው ህዝቡን በመልካም አስተዳደር እጦት እያማረሩ ያሉትን ተቋማትና አመራሮች በማጋለጥ ለውጡን ለማሳካት እንዲጥር አሳስባለች። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ)11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔውን ከመስከረም 23-25/2011 በሐዋሳ ከተማ ማካሄዱ ይታወሳል።