ወጣቶች የተረከቧትን አገር ሰላሟን ጠብቀው ለትውልድ ማስተላለፍ አለባቸው - የሲዳማ አገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች የተረከቧትን አገር ሰላሟን ጠብቀው ለትውልድ ማስተላለፍ አለባቸው - የሲዳማ አገር ሽማግሌዎች
አዲስ አበባ መስከረም 27/2011 ወጣቶች ከአባቶቻቸው የተረከቧትን አገር ሰላሟን ጠብቀው ለትወልድ ማስተላለፍ እንዳለባቸው የሲዳማ አገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቀረቡ። 11ኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ጉባኤ ትናንት በሐዋሳ ስታዲየም በተካሄደው የሲዳማ አባቶች የምረቃ እና መልካም ምኞት መግለጫ ስነስርዓት 'ቄጤላ' ፍጻሜውን አግኝቷል። በስነስርዓቱም አባቶች ለግንባሩ አዲስ አመራሮች መልካም የስራ ዘመን የተመኙ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ሰላም አስጠብቀው እንዲመሩም ጥሪ አቅርበውላቸዋል። ኢዜአ በስፍራው ተግኝቶ ያነጋገራቸው የሲዳማ አገር ሽማግሌዎች እንዳሉት፤ አባቶች እርስ በርስ በመዋደድ ለወጣቶች ያስረከቧት አገር ሰላሟ ተጠብቆ ለመጪው ትውልድ መሸጋገር አለባት። አቶ ታፈሰ ኦሪሶ ወጣቶች ከአባቶቹ በተሻለ ለአገር ሰላም ዘብ እንዲቆሙና የአገር ሰላምን ለማወክ በሚሰሩ አካላት እንዳይታለሉ መጠንቀቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ወጣቶች ከአባቶቻቸው ተምረው ጸብና መገፋፋት እንዳይኖር የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ ክፍሌ አከና ናቸው። ወጣቶች ወደፊት ብሩህ ተስፋ ስለሚጠብቃቸው ለአገር ሰላምና አንድነት ከማናቸውም በላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። አጂ ኤባ በበኩላቸው የአገር ሽማግሌዎች ለወጣቶች ትክክለኛ መንገድ ማሳየት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ወጣቶችም ታላላቆቻቸውን እንዲሰሙ ጥሪ አቅርበዋል።