ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የተሰማሩ የጥጥ እርሻ ባለሀብቶች የሰራተኛ አያያዛቸውን እንዲያስተካክሉ ተጠየቀ

አፋር መስከረም 27/2011 በአፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ የጥጥ እርሻ ባለሀብቶች የሰራተኛ አያያዛቸውን እንዲያስተካክሉ የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጠየቀ፡፡ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስትና የክልል የስራ ሃላፊዎች በወረዳው ውስጥ የሚገኙ የጥጥ ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡ በዚሁ ወቅት የጥጥ ልማቱ ላይ በስራ ተሰማርተው የሚገኙ ሰራተኞች አያያዝና ሁኔታ ላይ ቅኝት ተደርጓል፡፡ የአፋር ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተወካይ አቶ ሁሴን መሐመድ በክልሉ የሚገኙ የጥጥ ልማት ባለሀብቶች የሰራተኛ አያያዝ በተደጋጋሚ ችግር እንደሚታይበት ተናግረዋል፡፡ ለሚሰራው ስራ ተገቢ ክፍያ ያለመስጠት፣ የንፁህ ምግብና መጠጥ አገልግሎት አለመኖር፣ የመጸዳጃ ቤት አለመኖርና የህክምና አገልግሎት ለሰራተኞች ያለመስጠት ችግር ጎልቶ እንደሚስተዋል የቢሮው ተወካይ ገልጸዋል። የጥጥ ልማቱ የሚከናወነው ከከተማ ወጣ ባለ አካባቢ በመሆኑ የልማቱ ባለቤቶች የሰራተኞችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚጠበቅባቸውን የመወጣት ግዴታ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። የጥጥ እርሻ ባለቤት የሆኑት ባለሃብቶች የሰራተኛውን መሰረታዊ ፍላጎት የማያሟሉ ከመሆናቸው የተነሳ በእርሻዎቹ ተሰማርተው የሚገኙ ሰራተኞች ለተለያየ ኢኮኖሚያዊና ጤና ችግሮች እየተጋለጡ እንደሆነ አቶ ሁሴን ጠቁመዋል፡፡ ከጥጥ እርሻ ልማት ባለሀብቶች ጋር በተደጋጋሚ የሰራተኛ አያያዛቸውን እንዲያስተካክሉ ምክክር ተደርጎ የተወሰነ መሻሻል የታየ ቢሆንም መሰረታዊ ችግሮቹ አሁንም እንዳልተፈቱ አረጋግጠዋል። የደቡብ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተወካይ አቶ ሙሉዓለም ዲማርኮ በበኩላቸው ከደቡብ ክልል ለስራ ብለው በርካታ ወጣቶች ወደ አፋር በኤጀንሲዎች በኩል እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ለስራ ቅጥር መጥተው የተለያዩ የጤና ችግር ገጥሟቸው፤ ህይወታቸውን እስከማጣት የሚደርሱበት ጊዜ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም በአፋር ክልል በጥጥ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለሰራተኞቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀ ባለመሆኑ ለተለያዩ ጤና ቀውሶች የሚጋለጡበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑን ተወካዩ ያነሳሉ፡፡ የአዋሽን ወንዝ ተከትለው የጥጥ ልማት እያከናወኑ ያሉ ባለሀብቶች ለሰራተኞቻቸው ንጹህ የመጠጥ ውሃ እያቀረቡ ባለመሆኑ የወንዙን ውሃ ለመጠጥ እየተጠቀሙ ለተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች የሚጋለጡት በርካቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሰራተኞቹ የመስሪያ ቁሳቁስ ስላልተሟላላቸው ለጥጥ ተክሉ ታስበው በሚረጩ ኬሚካሎች የተለያዩ ጤና ቀውሶች ሲያጋጥማቸው ህክምና እንደማያገኙ አቶ ሙሉዓለም ጠቅሰዋል፡፡ የህይወት ኢንሹራንስም ስለሌላቸው፤ ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚወድቁም ተነግሯል፡፡ የእርሻ ልማት ስራ አስኪያጆቹ በበኩላቸው ያሉትን ክፍተቶች ከጥጥ እርሻ ባለሀብቶቹ ጋር በመመካከር መፍትሔ እንዲያገኙ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጥጥ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ በዘርፉ የተሰማሩ አንዳንድ ባለሀብቶች የሰራተኛ አያያዝ ችግር የሚስተዋልባቸው መሆኑን ተናግረዋል። በጥጥ ዘርፉ ባለሀብቶች ለሰራተኞቻቸው ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ባለሀብቶቹ ጋር የቅርብ ምክክር ተደርጎ ችግሮቹ በአጭር ጊዜ የሚስተካከልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም