የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በስትራቴጂ የታገዘ ስራ እየተከናወነ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በስትራቴጂ የታገዘ ስራ እየተከናወነ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ

ባህር ዳር (ኢዜአ) የካቲት 24/2015 የግብርናው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በስትራቴጂ የታገዘ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ዛሬ 241 የእርሻ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች አስረክቧል።
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በወቅቱ እንደገለጹት ባለፉት አመታት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት የተሰጠ ቢሆንም አሰራሩ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ በኩል ለውጥ ሳይመጣ ቆይቷል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በስትራቴጂ የታገዘ ስራ እየተከናወነ ነው።
ከቅርብ አመታት ወዲህ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በተግባር የታገዘ ለውጥ የሚያመጣ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በስንዴና አኩሪ አተር ምርት በክልሉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የአርሶ አደሩን ጊዜ የሚቆጥቡና የምርት ብክነትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን በረጅም ጊዜ የብድር አቅርቦት በማመቻቸት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
አርሶ አደሩን በቴክኖሎጂ የማዘመንና በረጅም ጊዜ ክፍያ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች እንዲያገኝ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በተለመደው መንገድ መሄድ እንደማያዋጣ የገለጹት ደግሞ የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ናቸው።
የግብርና ምርታማነትን በፍጥነት ለማሳደግ ዘመኑ ያፈራቸውን ጊዜ ቆጣቢና የአርሶ አደሩን ድካም የሚቀንሱ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ባለፉት ዓመታት መንግስት የግብርናውን ዘርፍ የሚያዘምኑ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የእርሻ ቴክኖሎጂዎች ከቀረጥ ነጻ እያስገባ መሆኑን ተናግረዋል።
በሃገር አቀፍ ደረጃ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ብዙ እንደሚቀር የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከሚታረሰው መሬት 22 በመቶው ብቻ በትራክተር እየታረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን አስቻይ ሁኔታዎች መቅደም እንዳለባቸው አመልክተው፤ ለዚህም አንዱና ዋነኛው መሬትን በኩታ ገጠም ማረስ እንደሆነ አብራርተዋል።
ለዚህም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን የተናገሩት ዶክተር ግርማ፤ አሁን ላይ እንደ ሀገር 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ተደራጅቷል ብለዋል።

''አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማሪያም ከፍያለው ናቸው።
በክልሉ ለዓመታት የነበሩት ትራክተሮች ከ800 ያልበለጡ እንደነበሩ አስታውሰው፣ ባለፉት ሁለት ዙሮች ብቻ ከ700 በላይ ትራክተሮች ለአርሶ አደሮች ማስረከብ ተችሏል ብለዋል።
አሁን ላይ በዘር በመሸፈን ላይ ከሚገኘው 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት 11 በመቶው ብቻ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚታረስ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ለአርሶ አደሮች ትራክተሮችን የማቅረብና ሌሎች የማዘመን ጅምር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የክልሉ መንግስት በረጅም ጊዜ ክፍያ የትራክተር ባለቤት እንዲሆኑ ማድረጉ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደንብያ ወረዳ የመጡት አርሶ አደር አሰፋ አያሌው ናቸው።
አርሶ አደሮቹ የተረከቧቸው የእርሻ ትራክተሮች የተለያየ የፈረስ ጉልበት እንዳላቸው ተገልጿል።
በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የክልሉና የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።