ቀጥታ፡

በተያዘው ዓመት ሰባት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ይጠናቀቃል-ዶክተር አርከበ

አዲስ አበባ መስከረም 27/2011 በኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ሰባት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንደሚጠናቀቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰበሳቢ ዶክተር አርከበ ዕቁባይ ገለጹ። የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ የምረቃ ስነ ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል። ፓርኩ 2ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በዋናው የአዲስ አበባ ጂቡቲና የወጪ ንግድ መተላለፊያ ላይ የሚገኝ፤ ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልምድ ተወስዶ የተገነባ ነው። የቦርድ ሰበሳቢው ዶክተር አርከበ ዕቁባይ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ፓርኩ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኢቨስትመንት የሚያፈሱ ከደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና ሁናን ግዛትና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ባለሃብቶች ይስተናገዱበታል። ''ፓርኩ ከአፍሪካ ትላልቅ ከሚባሉት ፓርኮች መካከል አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል'' ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው የኢኮኖሚ እድገቱን ለማረጋገጥ የኢንዱስትሪ ልማት ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነ አመልክተዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻር  የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል። በመስኩ ውጤት ለማምጣት ትላልቅና ደረጃቸውን የጠበቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታና ማስፋፋት እንዲሁም አምራች ኢንቨስትመንትን መሳብና ማበረታታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የአይሲቲ ፓርክ ቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ፣ የሀዋሳ፣ መቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ያስታወሱት ዶክተር አርከበ በዚህ ዓመት ጥቂት ወራት ውስጥ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ ድሬዳዋ፣ የቂሊንጦ የመድሃኒት ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የቦሌ ለሚ ቁጥር 2፣ የጅማ፣ ባህዳርና ደብረ ብርሃን ተጠናቀው ወደ ማምረት እንደሚሸጋገሩ ጠቁመዋል። የአረርቲ፣ አይሻ፣ ሰመራ፣ አሶሳ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚገነባው የዩሮ ስፔስ ማኑፋክቸሪንግና የሁናን አዳማ የማሽን አምራች ኡንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በዚህ ዓመት የሚጀመር መሆኑንም ገልጸዋል። በክልሎች የሚገነቡት አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአልሚዎች የተገነቡና የሚለሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ እስከ 2012 በአጠቃላይ 30 የኢንዱስትሪ ፓርኮች በኢትዮጵያ እንደሚኖሩ ጠቁመዋል። ይህም የኢንዱስትሪ ልማትና የኤክስፖርትን እድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንሚኖራቸው አብራርተዋል። አሁን ላይ የተገነቡ ፓርኮች 60 ሺህ የማኑፋክቸሪንግ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን የገለጹት ዶክተር አርከበ ፓርኮቹ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጡ ቁልፍ የሆኑ ማነቆዎችን መፍታት ወሳኝ እንደሆነም አመልክተዋል። በሁሉም ፓርኮች ያጋጠመውን የኤሌክትሪክ አቅርቦች ችግር በፍጥነት መፍታት፣ የፓርኮች ኦፕሬሽንና አስተዳደር አቅምን ማሳደግ፣ ኤክስፖርትን ለማስፋፋት በሎጂሰቲክ፣ ጉምሩክ፣ ባንክና መሰል አገልግሎቶች ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብና ተሞክሯቸውን ለመቅሰምና ዘርፉን ለማሳደግ መንቀሳቀስ ተገቢ መሆኑንም አመላክተዋል። የአገር ውስጥ ባለሃብቶችም በመስኩ በስፋት እንዲሰማሩ በማድረግ በመንግስትና በባለሃብቶች መካከል ቅንጅት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ነው ዶክተር አርከበ አጽንኦት የሰጡት። ኢትዮጵያን በአፍሪካ የማኑፋቸሪንክ ማዕከል ለማደረግ የተያዘው ውጥን እንዲሳካም ዩኒቨርስቲዎች፣ ተቋማትና ህዝቡ የላቀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የአዳማ ህዝብና ወጣቶች የኢንዱስትሪ ፓርኩን እንደ አይን ብሌናቸው በመጠበቅና በመነከባከብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል። መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በልማት የሚነሱ ዜጎች ሙሉ በሙሉ የስራ እድል እንደሚፈጠርላቸው አረጋገጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም