ቀጥታ፡

የእንግሊዝ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ተጠየቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 24/2015 የእንግሊዝ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በሀገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ጥሪ አቀረቡ።

አምባሳደሩ በዌስት ሚኒስቴር የሁሉም ፓርቲዎች ፓርላሜንታዊ ቡድን አባላትና እንግዶች በተገኙበት ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም  የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዕድሎች ገለፃ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ እጅግ አዋጪ የሆኑ ሠፋፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ አግሮፕሮሰሲንግ፣ በኢነርጂ፣ በጤና፣ በቱሪዝም እና በማዕድን ዘርፎች ስለመሆኗ ጠቅሰዋል።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ ሪፎርሞች በመሥራት ሀገሪቱ ለውጪ ኢንቨስትመንትና ንግድ የበለጠ የተመቸ ሁኔታ የተፈጠረባት መሆኗን አንስተዋል፡፡

የንግድ ህግ ማሻሻያ፣ የካፒታል ገበያን ለመጀመር የህግ ማዕቀፍና ተቋም መፍጠር፣ የፋይናንስ ዘርፉ የውጪ ባንኮችን ተሣትፎ እንዲያካትት መደረግ፣ የኢንቨስትመንት ህግን ማበረታቻ ሥርዓት ማሻሻል፣ የቴሌኮም አገልግሎት ለግል ኢንቨስትመንት ክፍት መደረግ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው በለዋል።

በዚህም የተወሰኑ የእንግሊዝ ኩባንያዎች በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እየተሳተፉ ሲሆን የበለጠ እንዲሣተፉ የእንግሊዝ መንግስትም ማበረታታት እንደሚገባው ለፓርላማ አባላቱ ተገልጾላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም መንገደኞችን በ120 አገራት የሚያገናኝ የበረራ መረብ የፈጠረ ሲሆን ዕቃዎችንና ማጓጓዝ በተመለከተ በ60 ሀገራት የካርጎ አገልግሎት ተደራሽ እያደረገ መሆኑ ለባለሀብቶቹና ለንግዱ ማህበረሰብ ተጨማሪ ዕድል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በዌስት ሚኒስቴር የሁሉም ፓርቲዎች ፓርላሜንታዊ ቡድን ሰብሳቢ የፓርላማ አባል የሆኑት ሎርድ ሎረንስ ሮበርትሠንና ሚስተር ቲም ጆንሰን ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር እንዲሁም ሀገሪቱ ያላትን ዕድልና እያስመዘገበች ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት በማንሣት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የንግድ ልዑካን ቡድን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም