በኢትዮጵያ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ዩኤስ ኤይድ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ዩኤስ ኤይድ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 24/2015 የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስ ኤይድ) በኢትዮጵያ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የኤጀንሲው የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሲን ጆንስ የተራድኦ ድርጅቱ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልል ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያቀርብ መቆየቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ በፌደራል መንግስቱ እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የሰብዓዊ ድጋፉን ለማሳለጥ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ድጋፉ በዋናነት በውሃ አቅርቦት፣ በጤና አገልግሎት፣ በግብርና፣ በምግብ ዋስትና እንዲሁም በትምህርት ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።
የሰብዓዊ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ኤጀንሲው በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሕዝብ አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን በጋራ ማከናወን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከፌዴራል መንግሥት ጋር እየተወያየ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንንም ሃሳብ በመደገፍ “በቀጣይ የእኛ ጥረት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመሆን በመልሶ ግንባታ፣ መልሶ ማቋቋም ላይ የተያዘውን እቅድ ማገዝ ነው" ብለዋል ዳይሬክተሩ።
የአሜሪካ መንግስትና እና ዩኤስ ኤይድ በኢትዮጵያ የልማት መርሐ-ግብር በተለይም በጤና፣ በትምህርት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና በግብርና ላይ ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣይም የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን ልማት የመደገፍ እና ትብብርን የበለጠ የማጠናከር ስራዎች እንደሚሰሩ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።