ቀጥታ፡

የእንሰት አጠውልግ በሽታ የእንሰት ምርታማነት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑ ተገለጸ

ሶዶ(ኢዜአ) የካቲት 24/2015 የእንሰት አጠውልግ በሽታ በእንሰት ምርታማነት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

አገራዊ እና ክልላዊ የእንሰት ተክል አጠውልግ በሽታ መከላከያ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐግብር በወላይታ ሶዶ እየተካሄደ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን እንዳሉት፤ የእንሰት ምርት ለአርሶ አደሩ ቋሚ የገቢ ምንጭ እና ለምግብነት እንዲሁም ተረፈ ምርቱ ለእንስሳት መኖነት፣ ለቤት እና ለተለያዩ ቁሶች መስሪያነት በግብዓትነት በማገልገል ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።

ከዚህ ግልጋሎቱ ባለፈ እሴት በመጨመር ለኢንዱስትሪ ምርቶች በግብዓትነት በማዋል እና ለውጪ ገበያ በማቅረብ የኢትዮጵያን የውጪ ምንዛሪ ግኝት እያሳደገ ነው ብለዋል።

ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተክሉ ላይ እንሰት አጠውልግ የተሰኘ በሽታ በመከሰቱ ምክንያት በምርታማነቱ ላይ ተፅእኖ በማሳደር ቀላል የማይባል ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህንን ችግር ለመከላከል ንቅናቄ በመፍጠር የሕብረተሰብ ተሳትፎን መሰረት ያደረገ የእንሰት አጠውልግ በሽታ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት።

በተለይም የእንሰት ድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ጥራትን ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የእንሰት ምርት እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያሳድግ በመሆኑ እንደ ስንዴው በቁጭት በመነሳሳት ማልማት ከተቻለ የሚፈለገው ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።

የእንሰት አጠውልግ በሽታ በ'ዛንቶሞናስ ካምቴስትሪስ ፓቶቫር ሙሳሴረም' በሚባል የባክቴሪያ ተዋህስያን አማካኝነት የሚከሰትና በኢትዮጵያ ውስጥ እንሰትን ከሚያጠቁ በሽታዎች ዋንኛው እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የእንሰት ተክል በብዛት ከሚመረትባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደቡብ ክልል ቀዳሚ ሲሆን፤ተክሉ በአገሪቷ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የምግብ ፍጆታ እንደሚሸፍን ይገለጻል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም