ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገበችውን ድል የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ እንደግመዋለን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገበችውን ድል የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ እንደግመዋለን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 24/2015 ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገበችውን አኩሪ ድል የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ እንደግመዋለን ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ጎልተውና ደምቀው ከሚታወቁና ከሚታወሱ በርካታ የታሪክ ክስተቶች መካከል የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የተመዘገበው የዓድዋ ድል አንዱ ነው።
የዓድዋ ድል የኢጣሊያን ወራሪና ቅኝ ገዥ ኃይል ቅስም በመስበር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት ከማስከበሩ ባለፈ፤ ጥቁር ሕዝቦችን ቅኝ መግዛት እንደማይቻል ያስገነዘበ ነው።
ኢትዮጵያ የአንድነት፣ የጀግንነትና የፅናት ፍሬ በሆነው በዓድዋ ድል ዳር ድንብሯ ሳይደፈር ብትቆይም፤ ከድህነትና የኢኮኖሚ ጥገኝነት ግን መላቀቅ አልቻለችም።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የዓድዋ ድል የቀደሙት ጀግኖች በፈጸሙት አኩሪ ገድል ቀና ብለን እንድንሄድ ያስቻለ ነው ይላሉ።
በዓድዋ የዘመኑ ጀግኖች የሀገራቸውን የግዛት ሉዓላዊነት እንዳስከበሩት ሁሉ፤ የዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ ሌላ የራሱን ታሪክ መጻፍ እንዳለበት አንስተዋል።
በዚህ ዘመን ደግሞ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ድሉን ለመድገም ትልቅ ተጋድሎ እያደረገች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ከልመና ወጥታ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ገበያ መላክ መጀመሯ ትልቅ ታሪካዊ ድል መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከውጭ የኢኮኖሚ ጥገኝነት በመላቀቅ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ለማስከበር በስንዴ ልማት የተመዘገበውን ስኬት በሌሎች የግብርና መስኮች ለመድገም እየሰራን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገበችውን አኩሪ ድል በዘመናዊ ግብርና የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ እንደግመዋለን ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በስንዴ፣ በሩዝ፣ በገብስ ልማት በስፋት በመስራት የሀገር ውስጥ ፍጆታን ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል ምዕራፍ ውስጥ መገባቱን ገልጸዋል።
በመኸርና በመስኖ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የተቀናጀና ፈጣን ተግባራትን በማከናወን የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ በመሆን የአያቶቻችንን ታሪክ እንደግመዋለን ብለዋል።
በሀገር አቀፍ የታክስና የጉምሩክ ህግ ተገዥነት ንቅናቄ መድረክ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና ከድህነት መውጣት የምንችለው በተባበረ ክንዳችን ሃብቶችን በመጠቀም ማልማት ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በአድዋ ድል ያሳየነውን አይበገሬነት በተባበረ ክንዳችን አቅማችንን በመጠቀም የተሻለች አገር እንገንባ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።