ቀጥታ፡

ወጣቶች ትኩረታቸውን ወደልማት እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ

አዳማ መስከረም  27/2011 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ነጻነት እንዲረጋገጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ወጣቶች ከአሁን በኋላ ትኩረታቸውን  ወደልማት እንዲያዞሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪውን ያቀረቡት በ4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባውን የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዛሬ ሲመረቅ ባስተላለፉት መልዕክት ነው። በዚሁ መልዕክታቸው እንደገለፁት የኢትዮጵያ ወጣቶች  በአገሪቱ የፖለቲካ ነፃነትና ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብዙ ሲሰሩ ቆይተዋል። "ይህን ጥረት አድርጎ ያሸነፈው ሰው አሁን አገር ወደመገንባትና ልማት ካልዞረ 'የመታገል ሱስ' እንጂ አገር የመቀየር አላማ አለው ማለት አይቻልም" ብለዋል። በመሆኑም "አሁን በሙሉ ልብ የምንታገለው ድህነትን ማሸነፍ መሆን አለበት" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሳሰበዋል። ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ተብሎ መሬታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች የልማቱ ተጠቃሚነታቸው እንደሚረጋገጥም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ያስታወቁት። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሥራ እድል እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር ህይወታቸው ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ይሆን ዘንድ መንግስት በትኩረት የሚከታተል መሆኑንም ገልፀዋል። ከመሬታቸው የተነሱ አርሶአደሮችና ቤተሰቦቻቸው ሥራ መያዛቸውን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተከታትለው እንዲያረጋግጡም ዶክተር ዓበይ መመሪያ ሰጥተዋል። የልማት ተነሺዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በአዳማ የሚተገበረው መልሶ የማቋቋም ሥራ በሌሎች አካበቢዎችም መለመድ ያለበት ተግባር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ መስራት የሚሹ ከሆነ ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አረጋግጠዋል። በ100 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎለታል። በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባም ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይጥራል ተብሎ ይጠበቃል። የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት መዋእለ ንዋይ የሚያፈሱ የተለያዩ ዓለም አገራት ታዋቂ የጨርቃጨርቅ አምራች ኩባንያዎች ይሰማሩበታል ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ሰባት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደስራ እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም