የፓኪስታን ባለኃብቶች የንግድ ሉዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት እድል ለመጠቀም የፊታችን እሁድ አዲስ አበባ ይገባሉ - ኢዜአ አማርኛ
የፓኪስታን ባለኃብቶች የንግድ ሉዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት እድል ለመጠቀም የፊታችን እሁድ አዲስ አበባ ይገባሉ
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ የካቲት 24/2015 ከ80 በላይ የፓኪስታን ባለሀብቶችን ያቀፈ የንግድ ሉዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ መሆኑን በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር አስታወቁ።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመጣው የንግድ ሉዑክ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰተዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፤ የፓኪስታንን የንግድ ሉዑክ አመጣጥ በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ በፓኪስታን ኢምባሲዋን ከከፈተች 6 ወራት ማስቆጠሩን ጠቅሰው በዚሁ ጊዜ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወኗን ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ተጠቃሽ መሆኑን ገልፀው ይህን መሰረት በማድረግ ከ80 በላይ የፓኪስታን ባለኃብቶች የንግድ ሉዑካን ቡድን የፊታችን እሁድ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል ብለዋል።
የንግድ ሉዑኩ በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት እድልና የተለያዩ አማራጮች ለመጠቀም የሚመጣ መሆኑንም ነው የገለጹት አምባሳደሩ።
በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድናት፣ በቴክኖሎጂ፣ በጤና እና ሌሎችም የኢንቨስትመንት አማራጮች የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
የንግድ ሉዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ የአንድ ሳምንት ቆይታ የሚኖረው ሲሆን በቆይታው በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት እድሎችንና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይጎበኛል ብለዋል።
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ጠንካራ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ በተፈጠረው ተቋማዊ ግንኙነት ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት፣ የንግድ እና የቱሪዝም አቅም ማስገንዘብ ተችሏል ነው ያሉት።
በዚህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የወጭ ንግድን ለማሳደግ በሚያስችል ግንኙነት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ከፓኪስታን ጋር የነበረውን የ78 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ የወጭ ንግድ ወደ 200 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ያለው የሰው ኃይል አቅርቦት፣ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እንዲሁም የአንድ መስኮት አገልግሎት ኢትዮጵያ የውጭ ባለሃብቶችን እንድትስብ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።