በዓድዋ የታየውን የጀግንነት፣ የአንድነትና የነፃነት ወኔ በመላበስ የኢትዮጵያን ከፍታና ብልፅግና ማረጋገጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በዓድዋ የታየውን የጀግንነት፣ የአንድነትና የነፃነት ወኔ በመላበስ የኢትዮጵያን ከፍታና ብልፅግና ማረጋገጥ ይገባል
ደሴ (ኢዜአ) የካቲት 23/2015 ትውልዱ ጀግኖች አባቶች በዓድዋ ያሳዩትን የጀግንነት፣ የአንድነት፣ የአሸናፊነት እና የነፃነት ወኔ በመላበስ በተባበረ ክንድ የኢትዮጵያን ከፍታና ብልጽግና ማረጋገጥ እንዳለበት ተገለጸ።
127ኛው የአድዋ ድል በዓል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የክተት አዋጅ በተጠራበት ታሪካዊቷ ወረኢሉ ከተማ ተከብሯል።
የአማራ ብሔራዊ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ህሊና መብራቱ እንደገለጹት አገር ፈተና በገጠማት ጊዜ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ቆመው ፈተናውን በድል በማለፍ ለሌሎች ሀገራት ብርታትን፣ አልበገር ባይነትን፣ ጀግንነትንና አሸናፊነትን አስተምረዋል።
"በተለይ ኢትዮጵያ አበቃላት፣ ፈረሰች ሲባል ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን በማጠናከር በመስዋዕትነት አገርን ከነክብሯ ማስቀጠል ከቅድመ አያቶቻችን የወረስነው ስነ-ልቦና አለን" ብለዋል።
"የዛሬው ትውልድ ጀግኖች አባቶች በአድዋ ያሳዩትን የጀግንነት፣ የአንድነት፣ የአሸናፊነትና የነፃነት ወኔ ተላብሰን የኢትዮጵያን ከፍታና ብልጽግና ዳግም በተባበረ ክንድ ማረጋገጥ ይኖርብናል" ሲሉ ገልጸዋል።
ሃላፊዋ እንዳሉት የዓድዋ ድል በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግልና መስዋትነት የተገኘ ቢሆንም የመላው ጥቁር ህዝቦችና በቅኝ ግዛት የነበሩት ሁሉ ኩራትና የነፃነት ምልክት ነው።
የአሁኑ ትውልድ የዓድዋንና የጀግኖችን አንጸባራቂ ታሪክ በሚገባ አውቆ ድሉን ከመዘከር ባለፈ አንድነቱን አጽንቶ ድህነትን ማሸነፍ እንዳለበት መክረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ መስፍን መኮንን በበኩላቸው "የጋራ ደማቅ ታሪኮቻችንን ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ሃላፊነት ነው" ብለዋል።
"ዓድዋ በክብር የመኖራችን ምክንያት፣ የነፃነታችን ማረጋገጫ፣ የአፍሪካ ኩራት፣ የአሸናፊነት ስንቅና ሞራል በመሆኑ በየዓመቱ እንዘክረዋለን፣ እንማርበታለን" ብለዋል።
ከአድዋ ድል ብዙ መማር አለብን ያሉት ሃላፊው፣ ትውልዱም አባቶቹ ሀገር በክብር ያቆዩበትን መንገድ ተከትሎ ለኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
አቶ መስፍን በዞኑ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል።
ለእዚህም በውጫሌ ይስማ ንጉስ ከ35 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ ሙዚየምና ሀውልት መገንባቱን ነው የጠቀሱት።
"በአድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ በተጠራበት ወረኢሉ ከተማም ተመሳሳይ ሙዚየም ለመገንባት ታቅዶ እንቅስቃሴ ተጀምሯል" ብለዋል።